ሪፖርት | ደካማ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ ያለ ጎል ተቋጭቷል

የሊጉ የሁለተኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን እና አርባምንጭ ከተማ መካከል ተከናውኖ 0ለ0 ተጠናቋል።

በመጀመሪያው ሳምንት አራፊ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች በዝውውሩ ተሳትፈው ካስፈረሟቸው አዳዲስ ተጫዋቾች ሦስት በቋሚነት ይዘው ሲገቡ ባለፈው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው አርባምንጮች ቅጣት ባስተናገደው አበበ ጥላሁን ምትክ አካሉን አትሞን ተጠቅመው ጨዋታው ጀምሯል። ቀዝቀዝ ያሉ ፉክክሮችን እያስመለከተን በቀጠለው የቡድኖቹ ጨዋታ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴን መመልከት ብንችልም አርባምንጭ ከተማዎች አህመድ ሁሴንን የሚፈልጉ ኳሶች ላይ በይበልጥ ሲያተኩሩ ሳጥን ውስጥ በተወሰነ መልኩ የማጥቃት ግለታቸው ከፍ ያለ መልክ ነበረው።

በመልሶ ማጥቃት ወደ መስመር በሚለጠጡ ኳሶች በጥልቅ የጨዋታ መንገድ ማጥቃት ላይ የሚዳዱት መድኖች በአንፃሩ በተጋጣሚያቸው መጠነኛ ብልጫ የተወሰደባቸው ቢሆንም በ26ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ በግራ በኩል በቀጥታ መትቶ እድሪስ ኦጎዶጆ የተቆጣጠረው ቡድኑን በሙከራ ረገድ ቀዳሚ አድርጎታል። ዝግ ያሉ እና ደካማ እንቅስቃሴዎችን ብቻ እያስመለከተን ጨዋታው ቢቀጥልም አንድም ጥራት ያለው የግብ ዕድሎች ተፈጥረው ሳንመለከት በአመዛኙ ደካማ የነበረው የጨዋታ አጋማሽ ያለ ጎል ሊገባደድ ችሏል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ አርባምንጮች ማጥቃታቸው ላይ አሂዋብ ብሪያንን በፍቃዱ መኮንን በመተካት ማጥቃታቸው ላይ ዕድሳት አድርገው ተመልሰዋል። ያልተሻሻሉ ደካማ እንቅስቃሴዎች እየበረከቱ ቀጥለው በተወሰነ መልኩ በጨዋታ ሂደት አዞዎቹ የተጨማሪ ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ጨዋታውን የተቆጣጠሩ ቢመስልም በሁለተኛው አጋማሽ ለመጫወት የመረጡት ረጃጅም ኳሶቻቸው በአብዛኛው ባካኝ ነበር።

54ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከግራ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ወደ ጎል መቶ ኦጎዶጆ በያዘባቸው ሙከራን ያደረጉት መድኖች የጨዋታ ይዘታቸውን ከዳዊት እግር ስር መነሻን ባደረጉ እና ከተከላካይ ጀርባ በመጣል ለመጫወት ጥረቶችን ሲያደርጉ ቢስተዋልም እንደ ቡድኖቹ ደካማነት ሁሉ የግብ ዕድሎች የመፍጠር ተፅዕኖአቸው በእጅጉ ደካማ አቀራረብ የተላበሰ ነበር። ጨዋታው ተጠናቅቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ 90+5 ላይ የመድኑ ተከላካይ ዋንጫ ቱት ሙሉጌታ ካሳሁንን በክርን በመማታቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደበት ክስተት የጨዋታው ብቸኛ ትኩረት የሚስብ አጋጣሚ ሆኖ 0ለ0 በመጨረሻም ፍፃሜን አግኝቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ጥሩ የሚባል ጨወታ እንዳልሆነ እና እንዳሰቡት እንዳልሆነ ጠቁመው በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድናቸው አመርቂ አለመሆኑን በሁለተኛው አጋማሽ ግን የሚሻል መሆኑን ተናግረው ካለን የቡድን ችግር አንፃር ውጤቱ ተገቢ ነው በማለት በንግግራቸው ጠቆም አድርገዋል። የአርባምንጭ ከተማው  አሰልጣኝ በረከት ደሙ በበኩላቸው ጥሩ ጨዋታ እንደገጠማቸው ገልፀው ነገር ግን የባለፈውን ያህል እንቅስቃሴ ቡድናቸው ማድረግ አለመቻሉን ጥድፊያዎች በመኖራቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ በግለሰቦች ስህተት ዕድሎች መባከናቸውን እና በቀጣይም ለማረም እንደሚሰሩ ተናግረዋል።