የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተከላካይ ኢያሱ ለገሰ ያጋጠመው ጉዳት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ማጣራት አድርጋለች።
በሁለተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ እያደረጉት በነበረው ጨዋታ ገና በጨዋታው ጅማሬ ላይ ኢያሱ ለገሰ እና የቡድን አጋሩ ኪሩቤል ወንድሙ በራሳቸው የሜዳ ክፍል የመጣውን አደገኛ ኳስ ለማራቅ በሚያደርጉት ጥረት እርስ በእርስ በመጋጨታቸው እያሱ ለገሰ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስተናግድ ችሏል።
የሕክምና ባለሙያዎች ፈጥነው ወደ ሜዳ ገብተው የመጀመርያ ህክምና ያደረጉለት ሲሆን ለተሻለ ሕክምና በአምቡላንስ በአፋጣኝ ወደ ቀዳዴ አጠቃላይ ሆስፒታል አምርተዋል። በአሁኑ ወቅትም የሕክምና ምርመራውን በዛው ሆስፒታል እያደረገ ይገኛል። የጉዳቱ ሁኔታ የግራ እግሩ ከጉልበቱ በታች ያለው ሁለት አጥንቱ መሰበሩን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ተጫዋቹ ለተጨማሪ ሕክምና ነገ ጠዋት ወደ አዲስ አበባ እንደሚሄድ ያወቅን ሲሆን ከጉዳቱ ከባድነት በመነሳት ዳግም ወደ ሜዳ ለመመለስ ለረጅም ወራት የሕክምና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።