ሪፖርት | አዳማ ከተማ የሊጉን የመጀመሪያ ድል አሳክቷል

በምሽቱ ጨዋታ ስንታየሁ መንግስቱ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ አዳማ ከተማ ባህርዳር ከተማን 1ለ0 አሸንፏል።


የጣናው ሞገድ በወልዋሎ ላይ ካስመዘገቡት ድላቸው አቤል ማሙሽን በፍፁም ፍትሕአለው ብቻ ሲቀይሩ በአንፃሩ በስሑል ሽረ ሽንፈት አስተናግደው የመጡት አዳማ ከተማዎች በኩል ደግሞ የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ ሲደረግ በዚህም ሃይለሚካኤል አደፍርስ ፣ ኤልያስ ለገሠ ፣ አድናን ረሻድ እና ዳንኤል ደምሱ ወጥተው በምትካቸው ቻላቸው መንበሩ ፣ ጋዲሳ ዋዶ ፣ ሙሴ ኪሮስ እና ሙሴ ካቤላ በቋሚነት አስጀምረዋል።

በፌድራል ዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ መሪነት የጀመረው የምሽቱ ጨዋታ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት ባህርዳር ከተማዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ በአንፃሩ አዳማዎች የተጋጣሚያቸውን የቅብብል ስህተት አነፍንፈው በመንጠቅ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሞክረዋል።

በአጋማሹ ከተደረጉ ሙከራዎች ቀዳሚ በነበረው ሂደት11ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አንድ ሁለት ቢኒያም የሰጠውን ኳስ ነቢል ኑሪ በቀላሉ ግብ ቢያደርጋትም አወዛጋቢ በነበረ ዳኝነት ኳሷ ሳትፀድቅ ቀርታለች።

በቀጣዮቹም ደቂቃዎች ጨዋታውን በይበልጥ እየተቆጣጠሩ ይምጡ እንጂ ግልፅ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ውስንነት የሚታይባቸው ባህርዳሮች 13ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከፍሬዘር በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ዳግም ጋር ተገናኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ዳግም በግሩም ቅልጥፍና ኳሷን አምክኖበታል።

በእንቅስቃሴ ቢበለጡም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ ኳስን ከመረብ ለማገናኘት የተሻለ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አዳማ ከተማዎች ጥረታቸው ሳይሰምር አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጋዲሳ ዋዶን በአድናን ረሻድ ተክተው የተመለሱት አዳማ ከተማዎች በወሰዱት አንፃራዊ ብልጫ ተጋጣሚያቸው ላይ ጫናን የሚፈጥሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲሰነዝሩ ተስተውለዋል።

ይበልጥ ተነሳሽነታቸውን እያሳደጉ የመጡት እና በቀላሉ አድናን ዋነኛ የማጥቂያ መነሻ አድርገው መንቀሳቀስን የመረጡት አዳማዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ግብ አግኝተዋል።

ከእጅ ውርወራ መነሻዋን ያደረገችን ኳስ ከቅብብሎች በኋላ ከቀኝ ወደ ውስጥ አድናን ረሻድ ሲያሻግር የባህርዳር የመሐል ተከላካዮች ደካማ የቦታ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ነፃ ቦታ ላይ ሆኖ ኳሷን ያገኘው ስንታየሁ መንግስቱ በቀላሉ ወደ ግብነት ለውጦ አዳማ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ በሁለት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች በአንድ ደቂቃ ልዩነት በአቤል ማሙሽ እና ቸርነት ጉግሳ አማካኝነት አከታትለው ሙከራን ያደረጉት ባህር ዳሮች ጥረታቸው በዳግም ተፈራ መክኗል።

በመጠነኛ ፉክክር ለዘብ ባለ እንቅስቃሴ ጨዋታው ቢቀጥልም ግልፅ የሆኑ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩበት በመጨረሻም በአዳማ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አሰተያየቶች የባህርዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ገልፀው ቡድናቸው እንደ ቡድን አለመጫወቱን እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኙትን አጋጣሚዎችን መጠቀም እንዳልቻሉ ጠቁመው ከጨዋታው ትምህርት እንደሚወስዱ እና ተጋጣሚያቸውን ከነበረው ተነሳሽነት አንፃር ውጤቱ የሚበዛበት እንዳልሆነ በንግግራቸው ገልፀዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ በበኩላቸው እንደጠበቁት ጨዋታውን ማግኘታቸውን ገልፀው የተገኙትን ዕድሎች በመጀመሪያ አጋማሽ አልተጠቀምንም ካሉ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ ግን አሻሽለው ጥሩ ውጤትን ይዘው እንደወጡ ተናግረዋል።