ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በሲዳማ ቡና የበላይነት ተጠናቋል

በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው መርሃግብር ሲዳማ ቡና መቻልን በመርታት የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ መሉ ሦስት ነጥባቸውን አሳክተዋል።


መቻሎች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በፎርፌ አሸንፈው የመጡ ሲሆን በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በመክፈቻ ጨዋታቸው በሀዋሳ ከተረታው ስብስብ የአምስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አስቀድሞ በቅርቡ በሞት ለተለዩት አሰልጣኝ አዳነ ገብረየስ የአንድ ደቂቃ ፀሎት በማድረግ በጀመረው ጨዋታው ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያ ሙከራቸው ቀዳሚ ሆነዋል ፤ 2ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር መቻል ሳጥን ጠርዝ የደረሰውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ ማስቆጠር ችሏል።

በጊዜ ተመሪ ለመሆን የተገደዱት መቻሎች በጨዋታው ከፍ ያለ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ23ኛው ደቂቃም አቻ ሆነዋል ፤ ቀደም ብሎ ፍፁም ያለቀለት አጋጣሚን አምክኖ የነበረው ሽመልስ ከቀኝ መስመር የደረሰውን ኳስ ተረጋግቶ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

መቻሎች የበላይነት በተንፀባረቀበት አጋማሽ እንደበራቸው ብልጫ የጠሩ በቂ አጋጣሚዎችን ባይፈጥሩም አብዱልከሪም ወርቁ እና ዓለምብርሃን ያደረጓቸውን ሙከራዎች መስፍን ሙዜ አድኗቸዋል ፤ አንድ አቻ በተጠናቀቀው አጋማሽ አልፎ አልፎም ቢሆን በመልሶ ማጥቃት አደጋ መደቀን የቻሉት ሲዳማዎች በተለይ ሬድዋን ናስር ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ የመታት እና አልዌንዚ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበረች።

ቀዝቀዛ ያለ አጀማመር በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሂደት በጨዋታው ብልጫ ወስደው መጫወት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በ69ኛው ደቂቃ ዳግም መሪ መሆን ችለዋል ፤ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረው ይገዙ ቦጋለ ከቀኝ መስመር ተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።

መመራት የጀመሩት መቻሎች አቻ ለመሆን ከፍ ባለ ጥረት ባደረጉበት ቀሪ የጨዋታ ደቂቃዎች የሲዳማው የግብ ዘብ መስፍን ሙዜ የሚቀመስ አልሆነም በተለይ ከአብዱልከሪም ወርቁ እና አብዱ ሙታለቡ የተዘነዘሩበትን ሙከራዎች ያመከነበት መንገድ አስደናቂ ነበር።

በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ባለፈው ሳምንት አለመጫወታቸው ተፅዕኖ ስለመፍጠሩ አንስተው በቀጣይም ስህተቶቻቸውን ለማረም እንደሚሰሩ ገልፀዋል ፤ በአንፃሩ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ውጤቱ ጥሩ ቢሆንም በኳስ ቁጥጥር ረገድ ቡድናቸው ማሻሻል እንደሚገባው እና በማጥቂያ ሲሶ የሚታይባቸው ጥድፊያ በቀጣይ መታረም ይገባዋል ብለዋል።