በዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ያሬድ ብርሀኑ ከዕረፍት መልስ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ መቐለ 70 እንደርታ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1ለ0 በሆነ ውጤት መርታት ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዋሎን ከረታው ስብስብ ሳይለውጥ ሲቀርብ በአንፃሩ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የነበሩት መቐለ 70 እንደርታዎች በበኩላቸው ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ የዓብስራ ተስፋዬን በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ተክተው ቀርበዋል።
በፌድራል ዋና ዳኛ ሀብታሙ መንግስቴ መሪነት በጀመረው የሳምንቱ የመክፈቻ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በይበልጥ ወደ መስመሮች አዘንብለው መንቀሳቀስ መርጠው መንቀሳስን የመረጡ ሲሆን ከመስመር እንቅስቃሴ ባሻገር አልፎ አልፎም ቢሆን ከቆሙ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል።
በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎችን በተጋጣሚያቸው ተበልጠው የታዩት መቐለዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መግባት ችለዋል።
በሂደት ወደ ጨዋታው የገቡት መቐለዎች በአሸናፊ ሀፍቱ እና ያሬድ ከበደ ሳጥን ውስጥ ያገኙትን ግልፅ የማግባት ዕድሎች አከታትለው ቢሞክሩም የተመስገን ዮሐንስ ግሩም ብቃቶች ሁለቱም ኳሶች መረቡ ላይ ማረፍ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
ከዕረፍት መልስ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ የገቡት ሞዓብ አናብስቱ በፍጥነት ግብ አስቆጥረዋል ፤ 50ኛው ደቁቃ ላይ ሠለሞን ሀብቴ ከግራ በኩል የተገኘን የቅጣት ምት ሲያሻግር በተደጋጋሚ የማጥቂያ መነሻው ሆኖ ይታይ የነበረው ያሬድ ብርሀኑ በግንባር ገጭቶ ኳሷን ከመረብ ማዋሀድ ችሏል።
መጠነኛ ግለትን ተላብሶ በቀጠለው ጨዋታ ፈረሰኞቹ አሁንም በመስመሮች በተለይም ተገኑን በሚፈልጉ ኳሶች በተደጋጋሚ ሳጥን አካባቢ ቢገኙም የሚፈጥሯቸው ዕድሎችን ግን የመቐለን የመከላከል አጥር መሻገር አልቻሉም።
በአንፃሩ ቀዳሚ መሪነቱን ከተረከቡ ወዲህ ወጣ ገባ የሚል እንቅስቃሴን ያሳዩት መቐለዎች በሂደት በእጃቸው የገባው ነጥብ ላለማጣት በጥንቃቄ ሲጫወቱ ተስተውሏል በዚህም መሰረት መቐለዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግባቸውን ሴያስደፍሩ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ድላቸውን ማስመዝገብ ችለዋል።