መረጃዎች | 10ኛ የጨዋታ ቀን


የ3ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገም ሲቀጥሉ በዕለቱ የሚደረጉ ሁለት መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ስሑል ሽረ

በሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ የሰበሰቡትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይገመታል።

ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች የሰበሰቡት ዐፄዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን በማሸነፍ የጀመሩት የውድድር ዓመት በጥሩ ሁኔታ እየሄደላቸው ይገኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር አቻ የተለያዩት ፋሲሎች በሁለቱም ጨዋታዎች የተለመደው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚጥር አጨዋወት ተከትለዋል። ሆኖም የግብ ዕድሎች የመጠቀም በዋነኝነት ደግሞ የመልሶ ማጥቃቶች እና ፈጣን ሽግግሮች የመከላከል ድክመት የተስተዋለባቸው ሲሆን በነገው ጨዋታም  ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረገው ሽግግር የሚስተዋልባቸውን ክፍተቶች ማረም ቀዳሚ ሥራቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በሁለቱም ጨዋታዎች ከቆሙ ኳሶች ግቦችን ያስቆጠረው እና በማጥቃቱ ረገድ የአፈፃፀም ክፍተቶች የተስተዋለበት ቡድኑ በነገው ጨዋታ ጌታነህ ከበደ ከጉዳት መልስ ማግኘቱን ተከትሎ በብዙ መንገድ ይለወጣል ተብሎም ይገመታል።

ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ሰብስበው መልካም አጀማመር ያደረጉት ስሑል ሽረዎች ጥሩ አጀማመራቸውን ለማስቀጠል ከዐፄዎቹ ጋር ይጫወታሉ። በሁለቱም ጨዋታዎች በሽግግሮች ለማጥቃት የሚሞክር እንዲሁም የተሻለ የመከላከል ቅርፅ ያለው የጨዋታ መንገድ የተከተሉት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት በነገው ዕለትም ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ይከተላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከተጋጣሚያቸው የቀደሙ ጨዋታዎች አቀራረብ በመንተራስ በጨዋታው ለመልሶ ማጥቃቶች የተሻሉ ዕድሎችን ያገኛሉ ተብሎም ይገመታል። ሆኖም ባለፉት ጨዋታዎች ከተጋጣሚዎች ጋር ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበረው የአማካይ ክፍላቸው በነገው ጨዋታ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ይገመታል። ሆኖም በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ የወጣው ዩጋንዳዊው አጥቂ አሌክስ ኪታታ አገግሞ ለጨዋታ ዝግጁ መሆኑ በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ለውጥ ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።

የተሰረዘው እና በስሑል ሽረ የሁለት ለባዶ አሸናፊነት የተጠናቀቀውን የ2012 የውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በታሪካቸው ሁለት ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ በአንዱ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት፤ የ2011 የመጨረሻ መርሐግብር የነበረው ጨዋታም በአቻ ውጤት ተገባዷል። ፋሲል ከነማ አራት ግቦች ሲያስቆጥር ስሑል ሽረ አንድ ግብ አስቆጥሯል።

በዐፄዎቹ በኩል ጌታነህ ከበደ እና አሚር ሙደሲር ከጉዳታቸው አገግመው ልምምድ መጀመራቸውን ተከትሎ በነገው ጨዋታ ይሳተፋሉ ተብሎ ሲጠበቅ በመጨረሻው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገዱት ብሩክ አማኑኤል እና አንዋር ሙራድ እንዲሁም በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ግን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ ግልጋሎት አይሰጡም። ሀገራዊ ግዴታውን ለመወጣት ከሃያ ዓመት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚገኘው ዳግም አወቀም ሽረን ከሚገጥመው ስብስብ ውጭ ነው። ስሑል ሽረዎች የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ከሆነው ብርሃኑ አዳሙ ውጭ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስባቸው ይዘው የሚቀርቡ ሲሆን ዩጋንዳዊው አጥቂ አሌክስ ኪታታም ከአንድ ጨዋታ በኋላ ቡድኑን ዳግም ለማገልገል ዝግጁ ሆኗል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ ያላቸውን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ተመጣጣኝ እና ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከባለፈው የውድድር ዓመት ጀምሮ ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ ያላቸው ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ ‘ፕሮፋይል’ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀረ ቡድን ገንብተዋል። ባለፈው የውድድር ዓመት ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት እንዲሁም ስል የሽግግር አቀራረብ ያሳዩን ቡድኖቹ ዘንድሮም ብዙም ለውጥ ሳያደርጉ መቅረባቸው ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎም ጨዋታው ተመጣጣኝ እና ብዙም ግብ ላይስተናገድበት ይችላል ተብሎ ሲገመት ባህርዳር ከተማዎች ባሏቸው ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ አመቺ የሆኑ አማካዮች በውስን መልኩ ጨዋታውን የሚቆጣጠሩበት ዕድል አለ ተብሎም ይገመታል።

በመጀመርያው ጨዋታ ወልዋሎን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ዓመቱን የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ በሁለተኛው ሳምንት በአዳማ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ሲጠበቅ በነገው ጨዋታ ጠጣር ቡድን እንደመግጠማቸው በሁለቱም መርሐግብሮች በፊት መስመር ላይ የታየባቸውን የስልነት ችግር መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል። በሊጉ መክፈቻ መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ዓመቱን የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በበኩላቸው ዳግም በሚታወቁበት አቀራረብ ብቅ ብለዋል። ሦስት ነጥብ ባስመዘገበበት ጨዋታ በአመዛኙ በሽግግሮች እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረገው ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ በጎዶሎ መጫወቱ በጥብቅ እንዲከላከል እንዳስገደደው ቢታመንም በነገው ጨዋታም ከተጠቀሰው የተለመደው የቡድኑ አጨዋወት የለቀቀ አቀራረብ ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ስምንት ጊዜ ሲገናኙ ሀዲያ ሆሳዕና አራት፤ የጣና ሞገዶቹ ደግሞ ሦስት ጊዜ ስያሸንፉ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱ እኩል የግብ መጠን ያላቸው ሁለቱ ቡድኖቹ በሰባቱ ጨዋታዎች አምስት ግቦች በእኩሌታ አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት አልተካተተም)

የጣና ሞገዶቹ ከጉዳትም ሆነ ቅጣት ነፃ የሆነውን ስብስባቸው ይዘው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ ነብሮቹ ግን በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ በሀምሳ አምስተኛው ደቂቃ ላይ በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣው አስጨናቂ ፀጋዬን በቅጣት፤ በረከት ወልደዮሐንስን ደግሞ በግል ጉዳይ ምክንያት አያሰልፉም።