በሊጉ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ስሑል ሽረ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ
ሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
“ማሸነፍን አስበን ወደ ሜዳ ብንገባም ሜዳ ላይ በተግባር የነበረው ግን ያንን የሚያሳይ አይደለም” – አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
“አቻ መውጣችን ብዙም አይከፋም” – አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ
በሁለተኛው አጋማሽ በማጥቃቱ ስለነበረባቸው መቀዛቀዝ …
“በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ደስተኛ አይደለሁም በሁለተኛው አጋማሽም በይበልጥ ብልጫ አለን ግን ብዙም የጎል ዕድል ከመፍጠር ጋር ተያይዞ ብዙ ዕድልን መፍጠር አልቻልንም። እነርሱ በጣም አግሬሲቭ ናቸው ገድበው ነው የሚጫወቱት ከዚያ አንግል በጣም ታይት የነበረ ጨዋታ ነበር ተጫዋቾችን ማርክ እያደረጉ ስለሚጫወቱ ራሳችንን ነፃ ለማውጣት የሄድንበት መንገድ ብዙም አመርቂ አልነበረም ስለዚህ በተፈለገው ደረጃ ዕድሎችን መፍጠር ችለናል ማለት አልችልም።”
በሦስቱ ጨዋታዎች ከክፍት ጨዋታ ጎል ማስቆጠር አለመቻላቸው…
“ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ከዛሬው የተሻለ እንቅስቃሴ እንዳደረግን ይሰማኛል በተለይ የመቐለ ጨዋታ ምንም እንኳን አቻ ብንወጣም በብዙ ነገሮች የተሻለ ነገር ነበረው ዕድሎችን መፍጠር ላይም ችግሮች አልነበረም ፣ ዛሬ ግን ወደ ኋላ የሄድንበትን ነገር ነው ያየሁት እንግዲህ ቀናቶቹም ቅርብ ከመሆናቸውም አንፃር በዕርግጥ ጨዋታዎቹ ገና ናቸው ግን ተጫዋቾች ላይ በተለይ እነ ቢኒያም ላይ የሚታይ ነገር አለ።በዛሬውም ጨዋታ እንኳን ብዙ ብልጫ አለን ብዬ መናገር ባልችልም መጥፎ አይደለም። ብልጭ ድርግም የሚል እንቅስቃሴ ያለን ይመጣል አንዴ ደግሞ ይጠፋል ስለዚህ እርሱን ማስተካከል አለብን የነበረውም ጨዋታ ከዕለት ዕለት እያሳደግን መሄድ እንዳለብን ይሰማኛል ለዛ ደግሞ ይበልጥ እንሰራለን።”
ተከታታይ አቻ ውጤት ስለ ማስመዝገባቸው…
“እግር ኳስ እንግዲህ ከሦስት ነገሮች አያልፍም በዕርግጥ የዛሬው አቻ የሚያስቆጭ ነው ማለት አልችልም ለምን የተፈጠሩ ብዙ ዕድሎች አልነበሩም። ማሸነፍን አስበን ወደ ሜዳ ብንገባም ሜዳ ላይ በተግባር የነበረው ግን ያንን የሚያሳይ አይደለም በቀደም የነበረው ጨዋታ ግን ብዙም የሚያስከፋ አልነበረም ጥሩ ሙከራዎች ጥሩ ፍሰት የነበረው ጨዋታ ነበር የነበረው ፣ መጥፎ አይደለም እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ማሸነፍ ደግሞ ቶሎ እንመለሳለን ለቀሪ ጨዋታዎች ባሉ ጊዜያቶች በዛ ውስጥ ለመስራት እንሞክራለን ጉዳት ላይ ያሉ ተጫዋቾችም አሉ እነሱን ለመመለስ ጥረት እናደርጋለን ያ ከሆነ ማሸነፍ ብዙ ይከብደናል ብዬ አላስብም።”
አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት – ስሑል ሽረ
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ዕድሎችን አግኝተው ስላለመጠቀማቸው …
“ከባለፈው ጀምሮ የአጨራረስ ሁኔታዎች በጣም ብዙ ክፍተት እያሳየን ነው ያለነው ይሄንን በተሰጠን በዚህ ዕረፍት ሰዓት ላይ የአጨራረስ ክፍተታችንን አስተካክለን እንመጣለን የዛሬ ጨዋታ አጠቃላይ የነበረው ግን እጅግ በጣም ጠንካራ ሁለታችንም አራት ነጥብ ነው ይዘን ወደ መሪነት ለመሄድ ያደረግነው ጨዋታ እንደመሆነለ ለሁለታቸንም ወሳኝ ነበር በተለይ ለእኛ ምክንያቱም ለማሸነፍ ነበር የገባነው ፋሲል ከነማ በጣም ትልቅ እና ጠንካራ ቡድን ነው ለሻምፒዮንነት የሚወዳደር ክለብ ነው ስለዚህ አቻ መውጣችን ብዙም አይከፋም።”
ሰባት ተጫዋቾችን በሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ በቋሚነት መጠቀማቸው እና ስለ መከላከል ጥንካሬአቸው…
“የመከላከል መስመራቸንን በጣም ጠብቀህ የተቃራኒ ቡድንን ለማጥቃት የምትሄደው እና ራስህን ግልፅ አድርገህ ለመሄድ ስትሞክር የፋሲል ከነማ የመስመር እና የፊት አጥቂዎች በጣም ፈጣን እና ጠንካሮች ስለሆኑ እነርሱን ማቆም አለብን በተመሳሳይ የሀዋሳ ከተማን የፊት መስመር ካየሀቸው በጣም ፈጣኖች ናቸው አሁን የተጠቀምነውም ያንን ነው መጀመሪያ የተቃራኒ ቡድንን ጥልቀት ያለውን የማጥቃት ስራ ማስቆም ከዛ ቀጥሎ ደግሞ የራሳችንን ስትራቴጂ እና ታክቲክ ተጠቅመን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር አደረጃጀታችንና የሰባቱ ያየህው የመከላከል መንገድ አማካዩ ተከላካዩን እየተጠቀምኩበት ነው የጠንካራ ስራ ውጤትም ነው።”
እንደ አዲስ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመጡበት ዓመት ስላገኙት አምስት ነጥቦች …
“ቡድናችን በሊጉ አዲስ እንደመሆኑ አምስት ነጥብ ማግኘት ጥሩ ነው ለምን ከእኛ የተሻሉ ቡድኖች ናቸው ከእኛ ኋላ ያሉት ስለዚህ ከተጋጣሚ ጋር ቀድሞ እና በልጦ መገኘት ያስፈልጋል። በሊጉም ከእያንዳንዱ ጨዋታ አንድ ነጥብ መውሰድ በጣም ትልቅ ዋጋ አለው እና ከአሁን በኋላ ለምናደርገው ጨዋታ ፕላስ እያደረግን ለመሄድ እንጂ የምንጥለው ነገር አይኖርም ነጥብ አየጨመርን ስንሄድ ነው በሊጉ እንደ ዕቅዳችን በሊጉ መቆየት የምንችለው።”