መረጃዎች | 11ኛ የጨዋታ ቀን

በሦስተኛ ቀን የፕሪምየር ሊጉ ውሎ የሚደረጉ ሁለት መርሃግብሮች ዙርያ ተከታዮቹ መረጃዎች ቀርበዋል።


ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ

ቀን 10 ሰዓት ላይ በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸው የአቻ ውጤት ያስመዘገቡትን ሁለቱን የፕሪምየር ሊጉ መስራች ክለቦችን የሚያገናኘው ጨዋታ ይጠበቃል።

በመጀመርያው የሊግ ጨዋታቸው ላይ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር አቻ የተለያዩት ቡናማዎቹ በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚጥር እና የተደራጀ የኋላ ክፍል ያለው አቀራረብ አስመልክተውናል ፤ ሆኖም ቡድኑ የግብ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ የአፈፃፀም ችግሩ በጉልህ ታይቷል ፣ በነገው ጨዋታም በሁለቱም ጨዋታዎች በተለይም ከሲዳማ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ የተሻለ የመከላከል አደረጃጀት የነበረው ሀዋሳ ከተማ እንደመግጠማቸው የፊት መስመር ክፍተታቸው ቀርፈው መቅረብ ግድ ይላቸዋል።

ከሲዳማ ቡናው የመጀመሪያ የሊግ ድላቸው በኋላ በስሑል ሽረው ጨዋታ ወረድ ብለው የቀረቡት ሀዋሳ ከተማዎች ከመጨረሻ ጨዋታቸው የነበረባቸውን ስህተት ማረምን እያሰቡ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በማጥቃት ሽግግራቸው አደገኛ እንደሆነ እያሳየ የሚገኘው ቡድኑ በነገውም ጨዋታ የተለየ አቀራረብ ይዞ ይገባል ተብሎ ባይጠበቅም ግን ካለፈው ጨዋታ ላይ ያሳዩትን የመከላከል መዋቅር ማስተካከል ካልቻሉ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ በሚሰጠው ኢትዮጵያ ቡና መፈተናቸው አይቀርም።

ኢትዮጵያ ቡና በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋቾች አይኖርም በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች ዮሴፍ ታረቀኝ ፣ እንየው ካሳሁን እና አብዱልባሲጥ ከማልን በጉዳት መነሻነት ማሰለፋቸው አጠራጣሪ ነው።

ከሊጉ የተሳትፎ ዝርዝር ጠፍተው የማያውቁት ክለቦቹ ነገ ለ52ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና 17 ጊዜ ድል ሲያደርጉ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች 16 ድል አድርገዋል የተቀሩት 17 ግንኙነቶች ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተደመደሙ ነበሩ። ኢትዮጵያ ቡና 61 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 54 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

መቻል ከ ወላይታ ድቻ

ከሽንፈት ወደ ድል ለመምጣት የሚደረግ ፉክክርን በሚጠበቅበት የምሽቱ መርሃግብርን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ።

በሁለተኛው ሳምንት የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታን ለማድረግ የተገደዱት መቻሎች ከሲዳማ ቡናው ሽንፈት ለማገገም ሦስት ነጥብን በእጅጉ እየናፈቁ ወደ ሜዳ ይገባሉ። ኳስን መሠረት ባደረግ እና ከፍ ባለ የራስ መተማመን የፈጠራ ችግር የማይታይበት ቡድኑ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ በሲዳማው ጨዋታ ያሳዩትን የአፈፃፀም ድክመት መቅረፍ ከቻሉ አንዳች ነገርን ፈጥረው ሊወጡ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።

በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው የጨዋታ ሳምንት ግን አራት ግቦች ተቆጥረውባቸው ሽንፈት አስተናግደዋል። በነገው ጨዋታም በዋነኝነት በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በማጥቃቱ መልካም ቢሆንም የመከላከል መዋቅራቸው ላይ ግን በእጀጉ ማስተካከያዎችን አድርገው መቅረብ ግድ ይላቸዋል።

በመቻል በኩል ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር በዝግጅት ላይ የሚገኙት ግሩም ሀጎስ እና ዮሐንስ መንግሥቱ በነገው ጨዋታ የማይኖሩ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች ግን ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆነው ለጨዋታው ይቀርባሉ።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ አስራ ስምንት ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ስምንት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻሎች ደግሞ አምስት ጊዜ አሸንፈው በቀሪዎቹ አምስት ግንኙነቶች ደግሞ በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ነበሩ። የጦና ንቦቹ አስራ ሰባት እንዲሁም ጦሩ ደግሞ አስራ አራት ግቦችን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ማስቆጠር ችለዋል።