የጣና ሞገዶቹ የግራ መስመር ተከላካይ ለማስፈረም ተስማሙ

ባህር ዳር ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ ለማስፈረም ተስማምተዋል።

በአሰልጣኝ ደግአረጋል ይግዛው የሚመሩት ባህር ዳሮች የ2017 የውድድር ዘመንን ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታ ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ በመሸነፍ የሊጉን ጅማሬ ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ የኋላ ክፍላቸውን ለማጠናከር አንድ የግራ ተከላካይ ለማስፈረም መስማማታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለጣና ሞገዶቹ ለመጫወት የተስማማው ሐምሳሉ ጥላሁን መሆኑ ታውቋል። ከታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በዳሽን ቢራ በኋላ ለፋሲል ከነማ ያለፉትን ስምንት ዓመታት መጫወት የቻለው ታታሪው ተከላካይ በዐፄዎቹ ቤት በነበረው ቆይታ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ እና የሊጉን አንድ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።

ባለ ልምዱ ተከላካይ ወደ ባህር ዳር የሚያደርገውን ዝውውር የህክምና ምርመራ ማድረጉ ሲታወቅ በቀጣዮቹ ቀናት ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።