ሠራተኞቹ ከሊጉ መሰረዛችን ተገቢ አይደለም ሲሉ ይግባኝ ጠይቀዋል 

ወልቂጤ ከተማ የሊጉ የውድድር አመራር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ውሳኔ አስተላልፎብኛል ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።

አስገዳጅ የሆነውን የክለብ ላይሰንሲንግ ፍቃድ አለማግኘቱን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ በተከታታይ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች የፀደቀ የተጫዋቾች ስም ዝርዝር አለመላኩን ተከትሎ ፎርፌ መስጠቱን ተከትሎ ከውድድሩ መሰረዙን የሊጉ አክስዮን ማህበር ማሳወቁ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማ ከተማ ውሳኔውን በመቃወም ሁለት ገፅ የይግባኝ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብቷል።

በአቤቱታው መግቢያ ላይም ክለቡ ሲገልፅ በሊጉ ተሳታፊ ለመሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ክለብ ላይሰንሲንግ ክፍል ምዝገባ ማከናወን ግዴታ በመሆኑ እና ለነባር ተጫዋቾችም ሆነ አዲስ ለሚያስመዘግቧቸው ተጫዋቾች በደመወዛቸው ልክ እንሹራንስ እንዲገባ ፣ የተጫዋቾች ዕዳ እስከ መስከረም 8 2017 ካልተከፈለ የነጥብ ቅነሳ እንዲወሰን ፤ በተጨማሪም ይግባኝ ባይ ማሟላት ያለበትን ባለማሟላቱ በማስጠንቀቂያ እንዲታለፍ እና ታኅሣሥ 1 2017 በሚጀመረው የክለብ ፍቃድ አሰጣጥ ባለው ጊዜ እንዲሟላ ሆኖ በተሰጠው ጊዜ አሟልቶ ካልቀረበ በደንቡ መሠረት ተጨማሪ ውሳኔ እንደሚሰጥ ያመላከተው ክለቡ አዳዲስ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾችን በመያዝ ለአንድ ወር ያህል በዝግጅት ላይ ቆይቶ የተጫዋቾች ዕዳ በተለይም የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ክፍያ በውጪ ምንዛሬ የሚከፈል በመሆኑ ያንን ለመፈፀም ጥረት ቢያደርግም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገጠመው የውጪ ምንዛሬ እጥረት እና ገንዘቡ የሚከፈላቸው የውጪ ሀገር ተጫዋች አድራሻ አክቲቭ ባለመሆኑ በባንክ በኩል ሊከፈለው የሚገባው ክፍያ ተፈጻሚ ባለመሆኑ እና ይህም ከክለብ ላይሰንሲንግ ክፍል ማረጋገጫ ባለመሰጠቱ በሊጉ መሳተፍ አለመቻላቸውን ገልፀዋል።

“የሊጉ ውድድር አመራር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የወሰነውን ውሳኔ ለማሻር እፈልጋለሁ” ያለው የወልቂጤ ከተማ ስፖርት ክለብ ተከታዩን አንኳር ነጥብ አንስቷል።

1ኛ በሊጉ የውድድር አመራር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ የተፈፀመ የፍሬ ነገር እና የሕግ ስህተት ለአብነት ያህል

– ይግባኝ ባይ የምዝገባ ሂደት ማሟላቱ ሳይረጋገጥ እና ከፌዴሬሽን ማረጋገጫ ሳይገኝ በውድድሩ እንዲሳተፍ ፕሮግራም መውጣቱ ስህተት ስለመሆኑ

2ኛ ኮሚቴው ወልቂጤ ከተማን ከውድድር ለመሰረዝ የተጠቀመው መመሪያ ከተፈጠረው ጉዳይ ጋር ፈፅሞ ግንኙነት የሌለው ስለመሆኑ ማለትም

– ወልቂጤ በፌዴሬሽኑ የክለብ ላይሰንሲንግ ክፍል የሚከናወነውን የምዝገባ ሂደት አጠናቅቆ በፌዴሬሽኑ ማረጋገጫ ተሰጥቶት ወደ ውድድሩ አልገባም። ማረጋገጫ ተሰጥቶት ወደ ውድድር ያልገባን ክለብ ኮሚቴው የውድድር ፕሮግራም አውጥቶ በመመሪያው መሠረት አውጥቶ መቅጣቱ የዲሲፕሊን መመሪያውን የተፈጻሚነት ወሰን በግልጽ በመጣስ የተፈጸመ ሕገወጥ ተግባር በመሆኑ ይህ ሕግን መሠረት ያላደረገ ውሳኔ በመሆኑ ውሳኔው በይግባኝ ሰሚው ኮሚቴ ሊሻር ይገባል። ፎርፌ የሚሰጠው አንድ ክለብ በውድድሩ ሜዳ ባይቀርብ ፣ ቀርቦ ባይጫወት ፣ ለጊዜ ጨዋታ ቢያቋርጥ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ቢያቋርጥ ነው። ሆኖም ከፌዴሬሽኑ ማረጋገጫ ያላገኘን ክለብ በፎርፌ መቅጣት ከተጠቀሰው መመሪያ መቅጣት ተገቢ አለመሆኑን ፤


3ኛ ኮሚቴው በይግባኝ በቀረበለት አቤቱታ ላይ ምላሽ ሳይሰጥ ውሳኔ መስጠቱ ሕገወጥ ስለመሆኑ ማለትም የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉሥ መስከረም 16 2017 በኤፍ ኤም 97.1 ሬዲዮ ላይ ቀርበው ይግባኝ ባይ ከውድድሩ እንደሚሰረዝ መግለጫ መስጠታቸው ውሳኔው በአንድ ግለሰብ (በሰብሳቢው) ተፅዕኖ ብቻ በኮሚቴው ስም የተሰጠ ሕገወጥ ውሳኔ ስለመሆኑ አመላካች በመሆኑ ውሳኔው በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሊሻር እንደሚገባ አመላክቷል።