ሲዳማ ቡና በያሬድ ባየህ ብቸኛ ፍፁም ቅጣት ምት ግብ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን ካስመዘገበበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው – ሲዳማ ቡና
ጨዋታው እንዴት ነበር?
”ጨዋታው ጥሩ ነው። እነሱም ሶስተኛ ጨዋታቸው ላይ ነጥብ ላለመጣል የሞት ሽረት ነው ያደረጉት። ግን እኔ እንደታዘብኩት እጅግ ብዙ የግብ አጋጣሚዎችን አግኝተናል አንዳንዴም እድለኛ መሆን ይጠይቃል። ምናልባት አቻ ወጥተን ቢሆን ኖሮ ምን ሊሰማን እንደሚችል መገመት ይቻላል እና እጅግ እጅግ በጣም በርካታ ኳስ ነው ያመከንነው ፤ ዕድለኛ አልነበርንም። በመጨረሻው ሰዓት ፈጣሪ ስለፈቀደ አሸንፈናል ደስ ብሎኛል።”
እስከ አሁን ባሉት ሶስት ጨዋታዎች የፈጠሯቸውን ብዙ የግብ አጋጣሚ ስላለመጠቀማቸው እና ለማስተካከለ ስላሰቡት ነገር..?
”ልክ ነው። ብዙ አጋጣሚዎች ይገኛሉ፤ አሁን የአብዛኞቹ ችግሮች መነሻ ጥድፊያ ነው። ከሚገባው በላይ ጥድፊያ አለ ፤ ግቦችን ቶሎ ቶሎ ለማስቆጠር ፍላጎት አለ ነገር ግን በመረጋጋት ካልሆነ ኳስ ትንሽ ይከብዳል መረጋጋት ያስፈልጋል። የእኛ ተጫዋቾች የአቅም ችግር የለባቸው። ምክንያቱም የግብ አጋጣሚውን በመፍጠር ረገድ ችግር የለብንም ይሄንን ጥድፊያውን ትተን መረጋጋት መቻል አለብን።
በሦስቱም ጨዋታዎች ቡድንህን እንደምትፈልገው አግኝተኸዋል?
”አዎ ጥሩ ነው ፤ ወደ ትክክለኛው መንገድ መጥናል። መቶ ፕርሰንት ማለት አይደለም ግን በጣም ጥሩ ነው። ጥሩ ነው ሚያሰኘው አንደኛው ውጤቱ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ የእኛ ስኳድ እንደምታየው ሰፊ ስኳድ ነው ያለን በክህሎት የተሞሉ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች አሉን ስለዚህ እነዚህን በደንብ እየተጠቀምንበት ነው ያለው በየጨዋታው ተጫዋቾችን በማፈራረቅ ለመጠቀም እየሞከርን እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነው።”
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ
ስለጨዋታው
”ጥሩ ጨዋታ ነበር።”
አብዛኛውን ደቂቃ በራሳችሁ ሜዳ ስትከላከሉ የነበረበት ሂደት አቻ ፍለጋ ወይስ?
”አቻ ውጤት አይደለም። ያሰብነው በመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ ለመጨረስ ነበር እንዲያውም ያገኘናቸው የጎል አጋጣሚዎች በጣም በርካታ ነበሩ። ከዚያ በኋላ የድካም ስሜት አለ አዲስ የመጡ ተጫዋቾች የሰላሳ ደቂቃ ልምምድ ነው የሰሩትና በእነሱ በኩል ማድረግ ያለባቸውን አድርገዋል። እነሱን ተክተን ደግሞ ስንገባ በተወሰነ መልኩ አፈግፍገን የተጫወተንበት ምክንያቶች አሉ።”
ስለተሰጠው ፍፁም ቅጣት ዙርያ የሚሉት ካለ?
”እኔ የዳኞች ኮሚቴ አይደለሁም።”
እስከአሁን ባለው ሶስት ጨዋታ ቡድንህን እንዴት አየኸው?
”እየተስተካከለ እንደመጣ የሚያሳየን ነገር አለ። ተጨማሪ ሰዎችን እናገኛለን ብዬ አስባለሁ። እነዛ ነገሮች ሲስተካከሉ የተሻለ ቡድን ይወጣዋል ብዬ አሰባለሀ።”