ኢትዮጵያዊው አማካይ የዋልያዎችን ስብስብ መቼ ይቀላቀላል?

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ለሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጥሪ የተደረገለት ሱራፌል ዳኛቸው መቼ ቡድኑን እንደሚቀላቀል ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ጥቅምት 2 እና 5 ቀን ከጊኒ አቻው ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ከሀገር ውጭ እየተጫወቱ ጥሪ ካደረጉላቸው ተጫዋቾች መካከል በአሜሪካ የሚገኘው ሱራፌል ዳኛቸው አንዱ ነው።

እስካሁን ቡድኑ ባደረጋቸው ሦስት የልምምድ ቀናቶች ውስጥ ያልተገኘው ሱራፌል መቼ የዋልያዎቹ ስብስብን ይቀላቀላል ስትል ሶከር ኢትዮጵያ ማጣራት አድርጋ ተከታዩን መረጃ አግኝታለች።

ያሳለፍነው ዓመት መገባደጃ ላይ በሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ሀገሩን ካገለገለ በኋላ ወደ ክለቡ ሎውደን ዩናይትድ የተጓዘው ሱራፌል በአሁኑ ወቅት በዛው በአሜሪካ የሚገኝ ሲሆን ነገ ማክሰኞ ወደ ሀገር ቤት መጥቶ ረቡዕ ከቡድኑ ጋር ወደ አቢጃን እንደሚጓዝ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።