አምባሳደር መስፍን ቸርነት በስታዲየሞች ግንባታ ዙርያ ምላሽ ሰጥተዋል

ከደቂቃዎች በፊት ፍፃሜውን ባገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ፕሬዝደንት እና የፕሪምየር ሊግ አ.ማ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መቶ ዓለቃ ፍቃደ ማሞ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ስታዲየሞች ተገንብተው ውድድሮችን ማካሄድ ባለመቻለቸው ዙርያ ያላቸውን አቋም ማፀባረቃቸውን እና ጥያቄ ማቅረባቸውን አስቀድመን ባጋራናቹህ መረጃ አስነብበናችዋል።

በተነሳው ጥያቄ ዙርያ የኢፊድሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አምባሳደር መስፍን ቸርነት ምላሽ ሰጥተዋል።

“ከማዘውተሪያ ጋር በተገናኘ በሁላችሁም ተነስቷል ፤ የሚያልቁበት ሁኔታ ታይቶ ሀብትም ተመድቦ እየተሰራ ነው። እንደ አዲስ አበባ ስቴዲየም የካፍን መስፈርት አሟልቶ እንዲሰራ የተደረገው ስራ አዝጋሚ ነበር በሚፈልገው መልኩ አልሄደም የተባለው ትክክል ነው። በግልፅ ለመናገር በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በፌዴሬሽኑም መካከል የነበረው የአቋም ልዮነት የችግሩ ምክንያት ነው። በባለሙያዎች እና በፌዴሬሽኑም መካከል ቁርጥ ያለ ወጥ የሆነ መግባባት አልነበረም በግልፅ መናገር ስላለብኝ ነው። አሁን ችግሩ ተፈቷል ፤ ቢያንስ መደማመጥ የሚያስችሉ መስመሮች ላይ ነን የተሻሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው። መቶ ዓለቃ ፍቃደ ጉዳዩን ቀረብ ብለው ቢያዮት ጥሩ ነው። አዲስ አበባ ስታዲየም የካፍ መስፈርትን የሚያሟላበትን ብቁ የማድረግ ግዴታ አለብን ብለዋል።”

በማስከተል አምባሳደሩ ሀሳብ የሰጡበት የአደይ አበባ ስታዲየምን በተመለት ነበር ሲናገሩም “ከውጭ ሀገር የሚገኘው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በመንግስት ከፍተኛ በጀት ተመድቦ ስራውን እየተሰራ ነው። ስታዲየሙ በምዕራፍ የተከፋፈሉ ስራዎች ነው ያሉት በመሆኑ በዚያ መሠረት እየሄደ ይገኛል። ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት በትልቁ እየሰራች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ስታዲየሙን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ታስቧል።”

አምባሳደር መስፍን ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ “የክልል ስታዲየሞችን በተመለከተ እንደሚታወቀው ባለቤትነታቸው የክልሎች ነው። እኛ እዚህ ውስጥ ልንገባ አንችልም ሆኖም ድጋፍ እናደርጋለን እየተሰራ ያለውን ስራ እንከታተላለን።”ብለዋል።