ሪፖርት | ቀይ ቀበሮዎች በሦስት ሽንፈቶች ከውድድሩ ተሰናብተዋል

በ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታ ኢትዮጵያ በቡሩንዲ 3ለ2 ተረታ ያለምንም ነጥብ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።

በታንዛኒያዊቷ የመሐል ዳኛ ታቱ ኑሩ በተመራው የሁለቱ ቡድኖቹ የምድቡ ሦስተኛ መርሐግብር የመጀመሪያዎቹን አምስት ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በመድረስ በያሬድ ብሩክ አማካኝነት ከቅጣት ምት ሙከራን ቢያደርግም በመስመሮች በኩል በፈጣን ሽግግር አደገኛ መልክ በነበራቸው ቡሩንዲዎች በኩል ግን 7ኛው ደቂቃ ላይ ደስቲን ማኒሪሆ በግራ በኩል ወደ ሳጥን ኳስን ይዞ ወደ ሳጥን ሲገባ በግሩም ሀጎስ በመጠለፉ የዕለቱ ዳኛ የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ክሪስቶፍ ንዳይኬንጉሩኪዬ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ብዙም ግለት አልባ እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ ቀይ ቀበሮዎቹ ኳስን በማንሸራሸር መሐል ለመሐል ለአጥቂዎች ለማድረስ የሚደረጉ ጥረቶችን መጠቀም ከጀመሩ በኋላ በ25ኛው ደቂቃ ዋንጫ ቱት ከራስ ሜዳ እየገፋ የመጣውን ኳስ ያገኘው አምበሉ ያሬድ ብሩክ በጥሩ ዕይታ ጣጣውን ጨርሶ ሲያቀብለው አንተነህ ተፈራ ኢትዮጵያን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ አድርጓታል። ወደ አቻነት ከመጡ በኋላ በተዝናኖት በቅብብል ሳጥን ቶሎ ቶሎ የሚደርሱት ኢትዮጵያዎች በ28ኛው ደቂቃ በጨዋታው ልዩነት ሲፈጥር የተመለከትነው ያሬድ ብሩክ በጥሩ የእግር ስራ በግል ጥረቱ ያቀበለውን ኳስ ሚኪያስ ፀጋዬ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።

ከወገብ በላይ ጥሩ ሆነው ቢታዩም የኋላ መስመራቸውን ግን በእጅጉ ደካማ የነበሩት የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተጫዋቾች ተጋጣሚያቸው በሁለቱ መስመሮች በኩል በጥልቅ የጨዋታ መንገድ በተለይ ዴስቲን ማኒሪዮ በተሰለፈበት ግራው ክፍል በተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዝሩ መታየት የቻለ ሲሆን 34ኛው ደቂቃ ላይም ክሪስቶፍ ንዳይኬንጉሩኪዬ ለራሱ እና ለሀገሩ ሁለተኛ ጎል በማድረግ አጋማሹ 2ለ2 ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ በመጠነኛ መቀዛቀዝ ውስጥ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚመስል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ቡድኖቹ ቢያስመለክቱንም በተሻለ የማጥቃት ደመ ነፍስ በቀላሉ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በመድረሱ ረገድ ግን ቡሩንዲዎቹ ሻል ያለ መልክ ነበራቸው። ከአጋማሹ ጅማሮ አንስቶ ለሃያ አምስት ያህል ደቂቃዎች ብልጫውን ወስደው በሽግግር መጫወትን የመረጡት ቡሩንዲዎች ዘለግ ካሉ ቆይታዎች መልስ 71ኛው ደቂቃ ሪስቶፍ በግራ ይዞ ገብቶ የመታውን መስፍን ሙዜ የመከተበት እና እስማኤል ኒዮኪዊርዛ እና ደስቲን አከታትለው ያለቀላቸውን ዕድሎች ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ጫናን ፈጥረው መንቀሳቀስ የቻሉት ኢትዮጵያዎች በያሬድ ብሩክ እና አብዱሰላም የሱፍ አማካኝነት ጥራት ያላቸውን ዕድሎች ቢፈጥሩም በመከላከሉ የነበራቸው ደካማ የቦታ አያያዝ በመጨረሻም 86ኛው ደቂቃ ላይ ዴስቲን ማሪኒሆ ግሩም ግብን አክሎባቸው  ጨዋታው በመጨረሻም በቡሩንዲ 3ለ2 አሸናፊነት ተደምድሟል። ውጤቱን ተከትሎ ቀይ ቀበሮዎቹ ሦስቱንም የምድብ ጨዋታዎች ተሸንፈው ውድድራቸውን አጠናቅቀዋል።