ሪፖርት | ዋልያዎቹ አሁንም ሽንፈት አስተናግዋል

በ2025 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ሦስተኛ የማጣርያ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጊኒ አቻው የ4-1 ሽንፈት በማስተናገድ የማለፍ ዕድሉን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል።

ቀዝቃዛ አጀማመር በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጊኒዎች አንፃራዊ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በአንድ አጋጣሚ ሰዒድ ሀብታሙ በግሩም የጊዜ አጠባበቅ ካመከናት አጋጣሚ በቀር እምብዛም ሳቢ የነበረ እንቅስቃሴን በሜዳ ላይ አላስመለከተንም።

በከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር የታጀቡት ጊኒዎች በ17ኛው ደቂቃ ግን መሪ መሆን ችለዋል ፤ ሲርሆ ጊዩራሲ ከተከላካይ ጀርባ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ለመጠቀም ያደረገውን ጥረት ለማቋረጥ የሞከረው ብርሃኑ በቀለ በፈፀመው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት የቡሩሲያ ዶርቱሞንዱ አጥቂ ራሱ አስቆጥሮ ሀገሩን ቀዳሚ አድርጓል።

በተወሰነ መልኩ በጨዋታው ወጣ ገባ የሚልን እንቅስቃሴን ያደረጉት ዋልያዎቹ በአጋማሹ ሱራፌል ዳኛቸው ከቆመ ኳስ በቀጥታ ካደረጋት ሙከራ ባሻገር በተደራጀ መልኩ አደጋ ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት አናሳ ነበር።

በ34 ደቂቃ ከግራ መስመር ከተሻማ ኳስ በግንባሩ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረው ሲርሆ ጊዩራሲ በ37ኛው እና ጭማሪ ደቂቃ ላይ በግሩም ሁኔታ ከተከላካይ ጀርባ የደረሱትን ኳሶች እየነዳ በመግባት በተረጋጋ አጨራረስ በማስቆጠር አጋማሹ በጊኒ የ3-0 መሪነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ራምኬል ጀምስ እና ወገኔ ገዛኸኝን ቀይረው በማስገባት የጀመሩት ዋሊያዎቹ በአጋማሹ በፍጥነት ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል ፤ ከመሀል የተሻማለትን ኳስ ሰይዶባ ሲሴ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ሰዒድ ሀብታሙ መረብ ላይ በማሳረፍ የጊኒን መሪነት ወደ አራት አሳድጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም የተሻለ አጋማሽን ያሳለፉት ዋልያዎቹ ምንም እንኳን በሰፊ የግብ ልዩነት ቢመሩም ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል ፤ በ50ኛው ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ አመቻችቶ የሰጠውን ፍፁም ያለቀለት አጋጣሚ ቸርነት ጉግሳ ሳይጠቀምበት ሲቀር በ52ኛው ደቂቃ ግን በግሩም የቅብብል ሂደት ተጋጣሚ ሳጥን ያደረሱትን ኳስ ከነዓን ማርክነህ ማስቆጠር ችሏል።

በእንቅስቃሴ ረገድ ክፍት ሆኖ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሙሉ አቅሙ ለማጥቃት ሲጥር በሚተዋቸው ክፍት ቦታዎች ጊኒዎች ለመጠቀም ጥረት ያደረጉበት ነበር ፤ በዋልያዎቹ በኩል በ79ኛው ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ ያሻማውን ኳስ አቤል ያለው በግንባሩ በመግጨት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን ጨዋታው በጊኒዎች የ4-1 አሸናፊነት ሲቋጭ ውጤቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሁንም በአንድ ነጥብ እና በአምስት የግብ ዕዳ ከምድቡ ግርጌ ሲገኝ ጊኒዎች በአንፃሩ ዛሬ ባሳኩት የመጀመሪያ ድል በሦስት ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።