የአሰልጣኞች አስተያየት | ጊኒ 4 – 1 ኢትዮጵያ

👉”ድሉ ይገባቸዋል”

👉”ልዩነቱ ግልፅ ነው”

👉”በመከላከል አደረጃጀታችን ችግሮች ነበሩ”

በ2025 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ሦስተኛ የማጣርያ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጊኒ አቻው የ4-1 ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል።

ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋችሁ ያበቃለት ነው ማለት ይቻላል?

“እንደዛ ማለት አይቻልም፤ በሂሳባዊ ስሌት ያበቃለት ነው ማለት አይቻልም። ሦስት ቀሪ ጨዋታዎች አሉ ስለዚህ ገና ነው።”

ከጨዋታው በፊት ለማሸነፍ ነው የመጣነው ብለው ነበር በጨዋታው ምንድን ነው የተፈጠረው?

“አዎ፤ በእግር ኳስ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ነገር ይፈጠራል። ሁሉም ለማሸነፍ ነው የሚመጣው ለመሸነፍ አይደለም ስለዚህ እኛም ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው የመጣነው ምክንያቱም ከማሸነፍ ውጭ ዕድል አልነበረንም። ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል ግን ዕድለኛ አልነበርንም በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ችግሮች ነበሩብን። ጊኒዎችም ስህተቱን በሚገባ ተጠቅመውበታል ከዕረፍት በፊት ሦስት ግቦችን አስተናግደናል። በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ሞክረናል፤ እንደታየውም የሁለተኛው አጋማሽ ውጤት አንድ ለአንድ ነበር።”

ስለ ተቆጠሩት ግቦች ብዛት…

“ቀድሜ እንዳልኩት በመከላከል አደረጃጀታችን ችግሮች ነበሩ፤ ጥሩ አልነበረም። በተለይም የመሃል ተከላካዮቻችን በጥሩ የቦታ አያያዝ ላይ አልነበሩም። በአጠቃላይ ግን ጊኒዎች ከኛ የተሻለ ተንቀሳቅሰዋል፤ በመጀመርያው አጋማሽ ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል ስለዚህ ድሉ ይገባቸዋል።”

በጨዋታው ልዩነት የፈጠረው ነገር ምን ነበር?

“ልዩነቱን የፈጠረው ግልፅ ነው፤ እኛ ሦስት በውጭ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ነው ያሉን ጊኒ ግን በርከት ያሉ በውጭ የሚጫወቱ ተጫዋቾች አሏት። ልምድ፣ የታክቲክ አረዳዳቸው እና የቴክኒክ ብቃታቸውም ጥሩ ነው። ልዩነቱ ግልፅ ነው። በተለይም የመሃል ተጫዋቾቹ እና አጥቂዎቹን ካየን ጥሩ ናቸው ግዙፎችም ናቸው። ልዩነቱ ይህ ነበር።”