አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከነገው የጊኒ ሁለተኛ መርሐግብር በፊት ምን አሉ?

👉 “ዓላማችን ከጨዋታው ነጥብ መውሰድ ነበር።”

👉 “በእኛ በኩል በድክመታችን ላይ ስለሠራን የነገው ጨዋታ እንደ ባለፈው ይሆናል ብዬ አልጠብቅም ።”

👉 “ተጫዋቾቼ አንድ የሆነ ነገር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።”

👉 “እግርኳስ በቀመር የሚሰላ ባለመሆኑ የምናሰላው ቀመር አይኖርም። ኤ ሲደመር ቢ እኩል ይሆናል ሲ እና ሲ ሲቀነስ ቢ እኩል ይሆናል ኤ ዓይነት አይደለም።”

በአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ 4ለ1 ከረታው የጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር የመልሱን ጨዋታ ነገ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በኮትዲቫር ዳግም ያከናውናል። የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌም ከነገው የመልስ መርሐግብር በፊት የቅድመ ጨዋታ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ስለ ነገው ጨዋታ…?

“ምንም ዐዲስ ነገር የለውም። ዓላማችን ከጨዋታው ነጥብ መውሰድ ነበር ፤ ይህ እግርኳስ ነው። ባለፈው 4-1 ተሸንፈናል ያ ማለት ግን በሁለተኛውም ጨዋታ ይደገማል ማለት አይደለም ፤ በክፍተታችን ላይ ሠርተናል። በእግር ኳስ ምንም ነገር ይፈጠራል ፤ ባለፈው ጨዋታ ጨዋታውን ማኔጅ ለማድረግ የምንችለውን በሙሉ ሞክረናል።”

ለጨዋታ የተዘጋጃችሁት በምን ዓይነት መልኩ ነው…?

“በዚህኛው ጨዋታ ዙርያ ያን ያህል ጥልቅ መረጃን አልሰጣችሁም በአጠቃላይ ግን ከመጀመሪያው ጨዋታ የተለየ ነው የሚሆነው። እርግጥ ነው ክፍተቶች አሉብን ነገ ሌላ ቀን ነው ፤ ጊኒ ልምድ ያለው ቡድን ነው ቡድኑ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ነው 100% ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ቡድኑ የተዋቀረው ከሀገራቸው ውጭ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ነው የሚጫወቱት ደግሞ የሀገር ውስጥ ተጫዋቾችን ከሚጠቀም ብሔራዊ ቡድን ጋር ነው ነገር ግን እግርኳስ በዚህ ዓይነት መልኩ የሚከናወን አይደለም። የግለሰቦች ጉዳይ እንዳልሆነ ግልፅ ነው አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይሆናል ትልልቅ ቡድኖች ሳይቀሩ ብዙ ጎሎችን አስተናግደው ይሸነፋሉ ፤ ያ ማለት ግን እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ውጤቶች ሁልጊዜም ይከሰታሉ ማለት ደግሞ አይደለም።”

ባለፈው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከተፈጠሩት አንዳንድ አጋጣሚዎች ውጭ ያን ያህል በጨዋታው ላይ የተመለክተነው ነገር አልነበረም ፣ በዚህ ጨዋታ የተለየ ነገር እንመለከት ይሆን…?

“በሁሉም ረገድ ጥንቃቄ እናደርጋለን። ባለፈው ጨዋታ የጊኒን ቡድን በሚገባ ተመልክተናል። ቡድኑ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን ጨምሮ በትልልቅ ቡድኖች ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ይዟል እነኚህ ተጫዋቾች ቡድኑን በሚገባ አጠናክረዋል።  አሁን ግን ነገሩ ይለያል ቡድኑን ዐይተነዋል ፤ በእኛ በኩል በድክመታችን ላይ ስለሠራን የነገው ጨዋታ እንደ ባለፈው ይሆናል ብዬ አልጠብቅም ስለዚህ በተቻለን መጠን ግባችንን ሳናስደፍር ያለ ፍርሃት አጥቅተን በመጫወት ከዚህ ጨዋታ የሆነ ነጥብ መውሰድ ያስፈልገናል።”

ጨዋታውን ለማሸነፍ በእናንተ በኩል ቁልፉ ነገር ምንድን ነው…?

“ቁልፉን ነገር ልነግራችሁ አልችልም። እንደ አጠቃላይ ግን እንደ ቡድን ጨዋታውን መቆጣጠር እንፈልጋለን ፤ ተጫዋቾቼ አንድ የሆነ ነገር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል አጠቃላይ ባለው ነገር ለዚህ ጨዋታ ራሳችንን በሚገባ አዘጋጅተናል።”

ባለፈው ሦስት ጎል ስላስቆጠረባቸሁ ስለ ሴርሁ ጉይራሲ ምን ይላሉ…?

“ግዙፉ አጥቂ በቦሩሲያ ዶርትሙንድ እንደሚጫወት አውቃለሁ ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ተጫዋቾች መሐል አንዱ ነው። ሁሉንም ኳሊቲ አሟልቶ የያዘ ተጨዋች ነው ፈጣን እና ግዙፍ ነው በጭንቅላት ጎል ማስቆጠር ይችላል። በማንኛውም ሰዓት ልዩነት መፍጠር ይችላል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር አልነበረም። ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው የምለው በዚህ ምክንያት ነው።”

ለተጫዋቾቹ የመከሩት ምክር ምን ይሆን? ወደ አፍሪካ ዋንጫው የምትገቡስ ይመስላችኋል…?

“በነገው ጨዋታ ላይ ምንም ነገር ሊከሰት ይችላል ፣ እግርኳስ በቀመር የሚሰላ ባለመሆኑ የምናሰላው ቀመር አይኖርም ፣ ኤ ሲደመር ቢ እኩል ይሆናል ሲ እና ሲ ሲቀነስ ቢ እኩል ይሆናል ኤ ዓይነት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ይቀያየራሉ። በአጠቃላይ የሚያጠቃ እና ኦርጋናይዝድ በሆነ መልኩ የሚጫወት ቡድን ይኖረናል ፤ በእርግጠኝነት ካለፈው ጨዋታ የተለየ ይሆናል ግን በጥልቀት ስለቡድናችን የጨዋታ መንገድ መናገር አልፈልግም።”