የቀጥታ ስርጭት ጉዳይ ?

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ማን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይሰጣቸዋል ?

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምስል መብት ባለቤት የሆነው ሱፐር ስፖርት የመጀመርያዎቹ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት በቀጥታ አስተላልፎ የሦስተኛው ሳምንት መርሐ-ግብሮች ሽፋን አለመስጠቱ ይታወቃል። ያለፉትን አራት ዓመታት ሊጉን በብቸኝነት የቀጥታ ሽፋን የሰጠው ተቋሙ በውሉ የማብቂያ ዓመት ላይ ሽፋን የሚሰጣቸውን የጨዋታዎች ብዛት እንደሚቀንስ መገለፁም ይታወሳል። በዚህ መሰረት ምናልባትም ሊጉ በመጀመርያው ዙር የሱፐር ስፖርት የቀጥታ ሽፋን ላያገኝ እንደሚችል መረጃዎች እየወጡ ሲሆን የሊጉ የበላይ አካል እንደከዚ ቀደም በማሕበራዊ ትስስር ገፁ በቀጥታ እንደሚያስተላልፈውም ታውቋል።


የሦስተኛው ሳምንት ሙሉ ጨዋታዎች በፌስቡክ ገፁ ለተመልካቾች ማድረስ የቻለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ከዛሬ ጀምሮ መብቱን የገዛው ተቋም ወደ ቀጥታ ስርጭቱ እስኪመለስ ድረስ ጨዋታዎቹን በጥራት ለማድረስ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ሲገኝ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታዎች ከ ‘ኔትወርክ’ ጋር ተያይዞ የታየው ውስን የጥራት ችግር ለመቅረፍም ከቴሌኮም ተቋማት ጋር በመነጋገር ጨዋታዎቹን በተሻለ ጥራት ለማስተላለፍ በጥረት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።