እጅግ በርካታ ሙከራዎችን ያስመለከተን የሳምንቱ የመጀመርያ ጨዋታ በሀዋሳ አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በባህርዳር ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን ያሬድ በቀለ፣ መለሰ ሚሻሞ፣ በየነ ባንጃ እና ተመስገን ብርሃኑን አስወጥተው በሳማኪ ሚካኤል፣ አስጨናቂ ፀጋዬ፣ ሰመረ ሀፍታይ እና ፀጋአብ ግዛው ተክተው ሲገቡ ሀዋሳ ከተማዎችም ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ ሲሳይ ጋቾ፣ ማይክል ኦቱሉ፣ ግርማ በቀለ እና ቢኒያም በላይ በሰለሞን ወዴሳ፣ በረከት ሳሙኤል፣ አማኑኤል ጎበና፣ አቤኔዘር ዮሐንስ እና ተባረክ ሄፋሞ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ተቀራራቢ ፉክክር እና በአመዛኙ በመሃል ሜዳ በሚደረጉ ቅብብሎች ታጅቦ የተካሄደው የመጀመርያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። ሆኖም ያገኟቸውን ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም የተሻሉ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በዐሊ ሱሌይማን እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ካደረጉ በኋላ በስምንተኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስ ባስቆጠሩት ግብ መሪ መሆን ችለዋል፤ ከርቀት የተገኘችውን የቅጣት ምት ጎል በግሩም መንገድ ወደ ግብነት የቀየራትም አቤኔዘር ዮሐንስ ነበር። ሀዋሳዎች መሪ ካደረገቻቸው ግብ ከአራት ደቂቃዎች በኋላም በተለመደው የቡድኑ የፈጣን ሽግግር አጨዋወት መንገድ ግብ አስቆጥረው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ታፈሰ ሰለሞን በፈጣን ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ክልል የደረሰችውን ኳስ ለአጥቂው ዐሊ ሱሌይማን አቀብሎት አጥቂው በቀጥታ በመምታት ነበር ግቧን ያስቆጠረው።
ሁለት ግቦችን ካስተናገዱ በኋላ መጠነኛ ብልጫ የወሰዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ መውሰድ ቢችሉም ሳሙኤል ዮሐንስ ከቆመ ኳስ ከፈጠራቸው ዕድሎች ውጭ በክፍት የጨዋታ መንገድ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም።
በበርካታ ሙከራዎች የታጀበና ማራቂ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ነብሮቹ ፍፁም ብልጫ ወስደው የተጫወቱበት ሲሆን በአጋማሹም እጅግ በርካታ የግብ ሙከራዎች ያደረጉበት ነበር። በአንፃሩ በመጀመርያው አጋማሽ ሁለት ግቦች አስቆጥረው ጨዋታውን የመሩት ኃይቆቹ በሁለተኛው አጋማሽ ተዳክመው ታይተዋል። በአመዛኙ በቀኝ መስመር ከሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሀድያዎች አጋማሹ በተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ ካመከኗት ወርቃማ ዕድል በኋላ በሀምሳ አንደኛው ደቂቃ በፀጋአብ ግዛው አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። ተከላካዩ ከቆመ ኳስ ተሻምታ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች የጨረፏትን ኳስ በግሩም ሁኔታ መቶ ከመረብ ጋር በማዋሀድ ነበር ግቧን ያስቆጠረው።
ከግቧ በኋላም በርከት ያሉ ሙከራዎች ያደረጉት ሀድያዎች በተለይም በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ፍፁም ብልጫ ወስደው በርካታ የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። በተለይም በረከት ወንድሙ አሻምቷት በነፃ አቋቋም የነበረው ሰመረ ሀፍታይ መቶ ግብ ጠባቂው ያወጣት፤ ብሩክ በየነ ተጫዋቾች አታሎ መቷት ተከላካዮች ተረባርበው ያወጧት ኳስ እንዲሁም ራሱ ብሩክ በየነ ሰመረ ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት የግቡን አግዳሚ ለትማ የወጣችው ኳስ ነብሮቹን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ወርቃማ ዕድሎች ነበሩ። ሀድያዎች ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም መለሰ ሚሻሞ በሀዋሳዎች የኳስ አመሰራረት ስህተት ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት ሙከራ ሌላ አቻ የሚሆኑበት ዕድል አግኝተው አልተጠቀሙበትም።