የጨዋታ ሳምንቱ የመገባደጃ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ባህርዳር ከተማ
ኤሌክትሪክ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል፤ ባህርዳር ከተማ ደግሞ ሦስተኛ ድሉን ለማሳካት የሚደርጉት የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ነው።
በመክፈቻው ጨዋታ በወላይታ ድቻ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አቻ የተለያዩት ኤሌክትሪኮች በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ባህርዳር ከተማን ለማሸነፍ እንዲሁም የውድድር ዓመቱ አይን ገላጭ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳሳይ ጎል አልባ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ሦስት ግቦች አስተናግዶ ሽንፈት ካስተናገደ ወዲህ በተከታታይ ግቡን አለማስደፈሩ እንደ አወንታ የሚነሳለት ጉዳይ ቢሆንም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻለም። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በነገው ጨዋታ ባለፉት ጨዋታዎች ጥሩ ለውጦች ያሳየውን የመከላከል አደረጃጀት ጥንካሬ ከማስቀጠል በዘለለ የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ችግር መፍታት ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኙ ከመድን ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት መሰረት ቡድኑ አሁንም ለመከላከሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚገባ መገመት ይቻላል። ቡድኑ በዚህ አጨዋወት የሚዘልቅ ከሆነ ግን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች የመጠቀም ክፍተቱ በሚገባ መቅረፍ ግድ ይለዋል።
ከሦስት ጨዋታ ሁለት ድሎች እና አንድ ሽንፈት ያስተናዱት የጣና ሞገዶቹ ስድስት ነጥቦች ሰብስበዋል። ባከናወናቸው ጨዋታዎች በሁለቱ ግቡን ያስላስደፈረው እና አንድ ግብ የተመዘገበበት ቡድኑ የባለፈው የውድድር ዓመት ጥንካሬውን አስቀጥሏል። ጠጣሩ የመከላከል አደረጃጀትም የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ ነው። በነገው ጨዋታም በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግብ ያላስቆጠረውን ቡድን እንድመግጠማቸው የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ ይሆናል ተብሎ ባይገመትም በሂደት የተረጋጋው የኤሌክትሪክ የኋላ ክፍል ጥንካሬ ጨዋታው ተጠባቂ እንዲሆን ያደርገዋል።
ባካሄዷቸው ሦስት ጨዋታዎች በተመሳሳይ በሁለቱ ግባቸውን ያላስደፈሩና ተቀራራቢ የመከላከል ጥንካሬ ያላቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ በግቦች የታጀበና ክፍት ጨዋታ እንቅስቃሴ ይደረግበታል ተብሎም አይጠበቅም።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በስራ ፍቃድ ምክንያት ጨዋታ ሳያከናውን የቆየውን ጋናዊው ግብጠባቂ አብዱላሂ ኢድሪሱ ግልጋሎት ያገኛሉ፤ ሆኖም ሽመክት ጉግሳ በቅጣት እንዲሁም ገለታ ኃይሉ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰልፉም። በባህር ዳር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን የጣና ሞገዶቹ ሁለቱን ጨዋታዎች በድል ተወጥተዋል። በጨዋታዎቹ ባህርዳር ከተማ 5 ግቦች ስያስቆጥር ኤሌክትሪክ ሁለት ማስቆጠር ችሏል።
ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን
የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሃግብር የሆነው የሲዳማ ቡና እና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
በመጀመርያው የሊጉ ጨዋታቸው በሀዋሳ ከተማ የአንድ ለባዶ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ መቻል እና ወልዋሎን በተከታታይ አሸንፈው ስድስት ነጥቦች የሰበሰቡት ሲዳማ ቡናዎች ሦስተኛ ድላቸውን ፍለጋ መድንን ይገጥማሉ።
ቡድኑ መቻልን ካሸነፈበት የሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ ውጭ በተቀሩት ሁለት መርሃግብሮች በሁሉም ረገድ ፍፁም ብልጫ መውሰድ ቢችልም እንደሚፈጥረው የግብ ዕድሎች ማስቆጠር ግን አልቻለም። የግብ ዕድሎች በመፍጠርም ሆነ በመከላከሉ የተሻለ አቅም ያለው ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በነገው ዕለትም ተመሳሳይ የኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ የጨዋታ መንገድ ይከተላሉ ተብሎ ሲጠበቅ የቡድኑ የአፈፃፀም ክፍተት መቅረፍም ቀዳሚ ስራቸው እንደሚሆንም ይጠበቃል። ተጋጣሚያቸው መድን በሁለቱም ጨዋታዎች ግቡን ያላስደፈረ ቡድን መሆኑም የፊት መስመሩ ዕድሎች የመጠቀም ብቃቱን ከፍ አድርጎ እንዲገባ የሚያስገድደው ሌላ ምክንያት ነው።
ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦች የሰበሰቡት ኢትዮጵያ መድኖች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ።
በውድድር ዓመቱ ኳስና መረብ ያላገናኘው እንዲሁም ግብ ያላስተናገደው ቡድኑ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርቶ በወጣበት ጨዋታ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችልም የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ግን አመርቂ አፈፃፀም አልነበረውም። ቡድኑ በመጨረሻው መርሃግብር የገጠመው ኤሌክትሪክ በአመዛዡ መከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የተከተለ ነበር፤ ይህንን ተከትሎም ለኳስ ቁጥጥር አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረውለት ነበር። የነገው ተጋጣሚው ግን በተመሳሳይ ኳሱን ለመቆጣጠር የሚሞክር ቡድን እንደመሆኑ ከባለፈው ጨዋታ የተለየ ፈተና ይጠብቀዋል። በዚህም መሰረት ውስን የአጨዋወት ለውጥ የማድረጉ እና የተለመደው የፈጣን ሽግግር አጨዋወት የመከተሉ ዕድል የሰፋ ነው።
ሲዳማ ቡናዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም ከዚህ በተጨማሪ በስራ ፍቃድ ምክንያት ባለፉት ጨዋታዎች ያልተሳተፈው ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ቶም ኢካራም ለጨዋታው ዝግጁ ነው። በኢትዮጵያ መድን በኩልም ተከላካዮቹ ዋንጫ ቱት እና ሚሊዮን ሰለሞን ቅጣታቸውን ያላጠናቀቁ ሲሆን ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት አለን ካይዋ፣ መሀመድ አበራ እና ያሬድ ካሳዬ ጋር በመሆን የነገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሊጉ 10 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 4 ጊዜ ሲያሸንፍ 5 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተለያይተው ኢትዮጵያ መድን ደግም 1 ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ሁለቱም ቡድኖች እኩል 8 ግቦች አስቆጥረዋል።