በ2024 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚያደርጉትን ጨዋታ በተመለከተ ማጣራት አድርገናል።
ባሳለፍነው ሳምንት የ2024 የቻን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል በግብፅ ካይሮ መውጣቱ ይታወቃል። ሀገራችን ኢትዮጵያም በማጣሪያው በመጀመሪያው ዙር ከኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ጋር መደልደሏ ይታወሳል።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እሁድ ጥቅምት 17 ለማድረግ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሜዳ ፍቃድ ለማግኘት ለካፍ ጥያቄ ማቅረቡ ሲታወቅ በአሁኑ ሰዓት ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሆነና ምላሹ በዛሬው ዕለት እንደሚታወቅ ሶከር ኢትዮጵያ ከመረጃ ምንጮቿ አረጋግጣለች። ምናልባት የአዲስ አበባ ስታዲየም ፍቃድ የማያገኝ ከሆነ ጨዋታው ወደ ሌሎች የጎረቤት ሀገራት አምርቶ ሊደረግ እንደሚችል ታውቋል።
ኤርትራ ከዚህ በፊት በመሰል ውድድሮች ራሷን ስታገል ቢታይም ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታዋን በሜዳዋ ማከናወን ስለማትችል በታንዛኒያ/ዛንዚባር ለመለወን ዝግጅት ላይ መሆኗ ተሰምቷል። ጨዋታውም ከጥቅምት 22-24 ባሉት ቀናት እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በቀጣይ በዋና አሰልጣኝነት ቡድኑን ማን ይመራዋል? ዝግጅቱስ መቼ ይጀምራል? በማለት ባደረግነው ማጣራት አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ውላቸውን ለመጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ ያላቸው በመሆኑ ቡድኑን ይመራሉ ተብሎ ሲገመት የተጫዋቾች መረጣም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ሊጉ በማይቋረጥበት ሁኔታ በዚህ አጭር ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ መታሰቡን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
* በሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገውን ጨዋታ በተመለከተ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።