መረጃዎች | 17ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉን የአምስተኛ ሳምንት የመክፈቻ ሁለት ጨዋታዎችን በተመለከተ ተከታዩን ጥንቅር አሰናድተናል።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በጨዋታ ሳምንቱ በሁለት ነጥቦች ልዩነት የሚገኙትን ሁለቱን ክለቦችን የሚያገናኘውን ቀዳሚ ጨዋታ እንመለከታለን።

በሊጉ ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ፣ በሁለት አቻ እና በአንድ ድል በአምስት ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ ላይ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች በነገው ጨዋታ የዓመቱን ሁለተኛ ድል ለማስመዝገብ ከጠንካራው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ይፋለማሉ።
ከሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ በመቀጠል ባደረጓቸው ሦሰት ጨዋታዎች ላይ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ሲያዘወትር የተስተዋለው ቡድኑ ምንም እንኳን ግቦችን ለማቆጠር የሚሄድበት መንገድ መሻሻሎች ቢያሳይም በተቃራኒው በመከላከሉ ረገድ ግን አሁንም መሻሻሎች ይፈልጋሌ።

በተለይም በጨዋታ የመገባደጃ ደቂቃዎች ይበልጥ ተጋላጭ እየሆነ ያለው የመከላከል አደረጃጀታቸው በነገው ዕለት በተሻለ መንገድ ችግሩን ቀርፎ መግባት ግድ ይለዋል።

ቡድኑ ነገ የሚገጥመው በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ያለውን ድሬዳዋ ከተማ እንደመሆኑም የመስመር ጥቃቶችን የመመከት አቅሙ ከፍ አድርጎ እንደሚገባ ይጠበቃል። ቡድኑ የዓብስራ ተስፋዬን ጨምሮ ቦና ዓሊ እና ኪሩቤል ኃይሉ ከጉዳት መልስ ማግኘቱም የተጫዋቾች ለውጥ አድርጎ እንደሚገባ ይገመታል።

በሊጉ ብዙ ግብ ካስቆጠሩ ሁለት ክለቦች መካከል አንዱ መሆን የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ መቐለን በሊጉ ታሪክ ለአምስተኛ ጊዜ ይገጥማሉ። ሁለት ድሎችን እስካሁን ያስመዘገው የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለው ቡድን ከመጨረሻ የአቻ ውጤት በኃላ ዳግም ወደ አሸናፊት ስነ ልቦና ለመመለስ ይጫወታሉ።ወጥ በሆነ የፈጣን የመስመር አጨዋወት ሰባት ጎሎችን በተጋጣሚ መረብ ላይ ያሳረፈው እና ሦስት ግብን ብቻ ያስተናገደው ቡድኑ ነገም የጨዋታ አቀራረብ ለውጥን ሳያደርግ እንደሚገባ ይገመታል። ነገር ግን ከጨዋታ ጨዋታ የማጥቃት አቅማቸው ከፍ እያደረጉ ከሚገኙት ሞዓም አናብስቱ ከባድ የሆነ ፉክክር ማስተናገዳቸው የማይቀር ይመስላል።

መቐለ 70 እንደርታዎች አሁንም የዮናስ ግርማይ እና መናፍ ዐወልን ግልጋሎት አያገኙም ፤ ሆኖም ጉዳት ላይ የቆዩት የዓብስራ ተስፋዬ ፣ ኪሩቤል ኃይሉ እና ቦና ዓሊ ግን ከጉዳት አገግመው ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል። በድሬዳዋ ከተማ በኩል መጠነኛ ጉዳት የገጠመው አማካዩ መስዑድ መሐመድን የማሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን ከቅጣትም ሆነ ጉዳት ነፃ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን አምስት ጊዜ ሲገናኙ መቐለዎቸሰ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ ብልጫውን ሲይዙ ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በሁለቱ ድል አስመዝግቧል። በግንኙነታቸውም ሞዓም አናብስቱ ስድስት ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው አራት ጎሎችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ፋሲል ከነማ

የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አንድ አንድ ጊዜ ያነሱ ክለቦችን የሚያገናኘውን የነገ ምሽቱ ጨዋታ ከሚጠበቁት የጨዋታ ሳምንቱ መርሃግብሮች አንዱ ነው።

ከአህጉራዊ ውድድሮች መልስ ሦስተኛውን የሊግ ጨዋታውን የሚያደርገው የአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገዱ ቡድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅዱስ ጊዮርጊስ ካስተናገዱት ሽንፈት ለማገገም ከሌላኛው ጠንካራ ቡድን ፋሲል ከነማ ጋር የሚገጥመው ቡድኑ ያለፈውን የጨዋታ ሳምንት የሚያስረሳ ሦስት ነጥብን ለማሳካት እያለመ ጨዋታውን ያከናውናል። በዋነኝነት ፈጠን ባሉ የመስመር ሽግግሮች ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶችን ሲጠቀም አልፎ አልፎም በጥልቀት ለመንቀሳቀስ ሲታትር የሚስተዋለው ቡድኑ ግቦችን ለማስቆጠር ባይቸገርም ያለፈው ጨዋታ ላይ እንዳስተዋልነው ለኋላ ክፍሉ ጥንቃቄን ጨምሮ የማይጫወት ከሆነ የሚገጥመው ፋሲል ከነማን ከመሆኑ አኳያ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታን ነገም እንደሚገጥመው መገመት አይከብድም።

ሦስት የአቻ ውጤቶችን ከአንድ ድል ጋር ያስመዘገበው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተው ፋሲል ከነማ ሁለተኛ የዓመቱ ድሉን ለማግኘት የአምናውን ሻምፒዮን ይገጥማል። አንድም ሽንፈት ያልገጠማቸው አፄዎቹ ለኳስ ቁጥጥሩ ቅድሚያውን በመስጠት ተጋጣሚ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ ብንመለከትም ወደ ሳጥን በመድረስ ተጋጣሚ መረብ ላይ ግቦችን ከማስቆጠር አንፃር ግን ውስንነቶች ይታይባቸዋል። አራት ጎሎችን በአራት ጨዋታ አስቆጥረው በተቃራኒው ሦስት ግቦችን ያስናገደውን የኋላ ክፍሉን ጭምር ማሻሻል እንደሚገባቸው መናገር ይቻላል ፣ ሆኖም ቡድኑ የመከላከል አጥሩን በአግባቡ የማይጠብቅ ከሆነ ስል በሆኑት የንግድ ባንክ አጥቂዎች መፈተኑ አይቀሬ ነው።
ከአምናው ቅጣቱ የተላለፈበት ዩጋንዳዊው አጥቂ ሳይመን ፒተር እና ኤፍሬም ታምራት በቅጣት ፈቱዲን ጀማል በበኩሉ በጉዳት አይኖሩም ፣ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ መጠነኛ ጉዳት ያስተናገዱት ፉዓድ ፈረጃ ፣ አዲስ ግደይ እና ባሲሩ ዑመር ግን የመጨረሻ ልምምዳቸው ላይ ስለተሳተፉ ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።

እስከ አሁን በሊጉ አምስት ያህል ጊዜ የተገናኙት ቡድኖች በአምስቱ ግንኙነታቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ፋሲል ከነማዎች በአንዱ አሸንፈዋል። ሀምራዊ ለባሾቹ አስር ግቦችን አፄዎቹ በአንፃሩ አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።