ያሬድ ብርሃኑ በተከታታይ አራተኛ መርሐግብር ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ ድል ተመልሰዋል።
መቐለ 70 እንደርታዎች ከመቻል ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ ብሩክ ሙሉጌታ እና ሔኖክ አንጃው በየአብሥራ ተስፋዬ እና ቦና ዓሊ ሲተኩ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ከስሑል ሽረ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ መስዑድ መሐመድን በአቤል አሰበ ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ሁለት የተለያዩ አጨዋወቶችን የሚከተሉ ቡድኖች ያገናኘውን እና ተቀራራቢ ፉክክር የታየበት የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በዋና ዳኛ ተከተል ተሾመ ሲመራ ድሬዳዋ ከተማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ መቐለ 70 እንደርታዎች በበኩላቸው በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር የጣሩበት ነበር። ጨዋታው በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃም መቐለዎች በያሬድ ብርሃኑ አማካኝነት በተጠቀሰው አጨዋወት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።
ግብ አስቆጣሪው ያሬድ ብርሃኑ ፤ ቦና ዓሊ ከድሬ ተጫዋቾች ነጥቆ የሰጠውን ኳስ ገፍቶ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው። ግቧም የያሬድ ብርሃኑ አራተኛ ተከታታይ ግብ ሆና ተመዝግባለች። ብርቱካናማዎቹ ከግቧ መቆጠር በኋላ ጨዋታውን በተሻለ መንገድ መቆጣጠር ቢችሉም እንደፈጠሩት ጫና ጥራት ያለው ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ሆኖም በቻርለስ ሙሴጌ በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም በሱራፌል ጌታቸው አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም አቡበከር ሻሚል አሻምቷት በመቐለ ተከላካዮች መዘናጋት ቻርለስ ሙሴጌ እግር የደረሰች እና አጥቂው መቶ ወደ ውጭ ያወጣት እና ሱራፌል መሀል ለመሀል በተደረገ የመልሶ ማጥቃት ያገኛት ኳስ መቶ ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ የተሻለ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
በአጋማሹ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት መቐለዎች በድሬ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት ተጠቅመው ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠርም ተቃርበው ነበር። ከመጀመርያው ግብ ተመሳሳይነት ባለው ሁኔታ የአብሥራ ተስፋዬ በተጫዋቾች የቅብብል ስህተት ያገኛትን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት መቶ ግብ ጠባቂው እንደምንም ያመከናት ኳስ እንዲሁም ያሬድ ከበደ የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ መቷት አሕመድ ረሺድ ጎል ከመሆን ያዳናት ሙከራ የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ።
በአጋማሹ ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ በዘለለ ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት ድሬዎች ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በቻርለስ ሙሴጌ አማካኝነት ሙከራ አድርገው ሶፎንያስ ሰይፈ መልሶበታል።
ተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች እና እነሱን ተከትለው በሚነፉ ፊሽካዎች ታጅቦ የተካሄደው እና ብርቱ የፉክክር መንፈስ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ገና በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ነበር ግብ የተስተናገደበት። በ47ኛው ደቂቃም በቀኝ መስመር በኩል በመሐመድኑር እና ሱራፌል ጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን የገባችው ኳስ ሱራፌል አሻግሯት አስራት ቱንጆ ከመረብ ጋር ቀላቅሏታል።
ከመጀመርያው አጋማሽ ጋር ተመሳሳይ መልክ በነበረው ሁለተኛው አርባ አምስት ድሬዎች የተሻለ ብልጫ ቢወስዱም በርከት ያሉ የጠሩ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። በሰባኛው ደቂቃም መቐለዎች ጨዋታውን በድጋሚ የሚመሩበት ዕድል አግኝተዋል። አሸናፊ ሐፍቱ አጥቂው ያሬድ ብርሃኑ ከጋናዊው ሸሪፍ መሐመድ በረዥሙ የተቀበላትን ኳስ ካመቻቸለት በኋላ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። መቐለዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በመቀጠል በ85ኛው ደቂቃ ላይም በፍፁም ቅጣት ምት ተጨማሪ ግን አስቆጥረዋል። ያሬድ ብርሃኑ በራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት በመቀየር ነበር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገው።
ተደጋጋሚ ጥፋቶች በታየበት ጨዋታ ከደቂቃዎች በኋላም በመቐለ ሳጥን በተሰራው ጥፋት ሸሪፍ መሐመድ የቀይ ካርድ ሰለባ ሲሆን ድሬዎችም የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል፤ መሐመድኑር ናስር ወደ ጎልነት ቀይሮም የግብ ልዩነቱ ወደ አንድ ዝቅ ማድረግ ችሏል።
ጠንካራ ፉክክር፣ የብርቱካናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም አይምሬው የምዓም አናብስት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የታየበት ጨዋታም በመቐለ 70 እንደርታ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።