ሪፖርት| ጦሩ ዳግም ወደ ድል ተመልሷል

መቻል ወልዋሎን ሦስት ለባዶ በማሸነፍ ከአንድ ጨዋታ በኋላ ወደ ድል ተመልሷል።
ወልዋሎዎች በሲዳማ ቡና ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አስራ አንድ ላይ አላዛር ሽመልስን በናትናኤል ዘለቀ ብቻ ተክተው ሲገቡ መቻሎች በበኩላቸው ከመቐለ ጋር አቻ ከተለያየው ቋሚ አሰላለፍ አስቻለው ታመነ፣ ዓለምብርሀን ይግዛው እና ሽመልስ በቀለ በነስረዲን ሀይሉ፣ ግሩም ሀጎስ እና አማኑኤል ዮሐንስ ተክተው ገብተዋል።

የመቻል ሙሉ ብልጫ በታየበት እና በሙከራዎች ታጅቦ የተካሄደው የዕለቱ የመጀመርያው ጨዋታ መቻሎች የኳሱ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ አቤል ነጋሽ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ዕድሎች ሲፈጥሩ በ4ኛው ደቂቃም ብልጫ በወሰዱበት መስመር ግብ አስቆጥረዋል።

አቤል ነጋሽ ከአብዱልከሪም ወርቁ የተቀበላትን ኳስ ወደ ሳጥኑ አሻግሯት የወልዋሎው ተከላካይ ታዬ ጋሻው ኳሷን ለማውጣት በሚያደርገው ጥረት ወደ ራሱ ግብ በማስቆጠር መቻሎች በጊዜ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በሁሉም ረገድ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች ከጎሉ በኋላም በአማኑኤል ዮሐንስ፣ በረከት ደስታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል፤ በተለይም በረከት ደስታ ከግራ መስመር እየገፋ ወደ ሳጥን ከገባ በኋላ መቷት የግቡን ቋሚ ለትማ የተመለሰች ኳስ የጦሩን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

በአጋማሹ ውጤታማ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ብልጫ የነበረባቸው መቻሎች በ41ኛው ደቂቃም በአጋማሹ ድንቅ ብቃቱን ባሳየው አቤል ነጋሽ አማካኝነት ተጨማሪ ግን አስቆጥረው መሪነታቸውን አጠናክረዋል። በረከት ደስታ ከተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በረዥሙ የተላከችለትን ኳስ በአግባቡ ከተቆጣጠረ በኋላ ተከላካዮችን አልፎ ወደ ሳጥን ያሻገራት ኳስ በነፃ አቋቋም የነበረው አቤል ነጋሽ በማስቆጠር ነበር ግቧን ያስቆጠረው።

በአጋማሹ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩት እና የመቻልን የመልሶ ማጥቃት ለመቋቋም ሲቸገሩ የታዩት ቢጫዎቹ በዳዋ ሆቴሳ፣ ቡልቻ ሹራ እና ጋዲሳ መብራቴ አማካኝነት ከርቀት በተሞከሩ ኳሶች ሦስት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ የመቻል ሙሉ ብልጫ በታየበት እና ጦሩ በቁጥር በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ባመከነበት ሁለተኛው አጋማሽ በሙከራዎች የታጀበ ነበር። ጋዲሳ መብራቴ ከግራ መስመር አሻምቷት በነፃ አቋቋም የነበረው ዳዋ ሆቴሳ በግንባር ያደረጋትና እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ የጀመረው አጋማሹ በመቻሎች በኩል በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር።

በተለይም በሀይሉ ግርማ በመልሶ ማጥቃት ያገኛትን ኳስ አፈትልኮ ወደ ሳጥን በመግባት ሞክሯት ተከላካዮች ያወጧት፤ ምንይሉ ወንድሙ በሁለተኛው አጋማሽ ኮከብ ከነበረው በረከት ደስታ የተቀበላትን ኳስ መቶ በረከት አማረ ያዳናት እና አብዱልከሪም ወርቁ በሁለት አጋጣሚዎች ወደ ግብነት ያልቀየራቸው ወርቃማ ዕድሎች የጦሩን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሴኮንዶች ሲቀሩትም በረከት ደስታ ከቀኝ መስመር የተሻማችውን ኳስ በግንባሩ አመቻችቶለት ዳንኤል ዳርጌ ወደ ግብነት በቀየራት የዕለቱ ሦስተኛ ግብ ጨዋታው በመቻል የሦስት ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።