ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የተመለሰው ዱራሜ ከተማ የአሰልጣኙን ውል ሲያራዝም የስምንት ተጫዋቾችን ዝውውርም አጠናቅቋል።
ባሳለፍነው ዓመት በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ተወዳዳሪ የነበረው ዱራሜ ከተማ ከምድቡ አምቦ ከተማን ተከትሎ በወረደበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደጉ ይታወሳል።
ክለቡ በከፍተኛ ሊጉ በምድብ “ሀ” ስር ተደልድሎ ነገ 8 ሰዓት ላይ ከሸገር ከተማ ጋር በመጫወት ውድድሩን የሚጀምር ሲሆን ክለቡ የአሰልጣኙን ውል ማራዘሙን እና የስምንት የተጫዋቾችን ዝውውር ማጠናቀቁን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።ውሉን ያራዘመው አሰልጣኝ አዲስ ዶይሶ (ወይዲዴ) ነው። በተጫዋችነት ለደቡብ ፖሊስ ፣ ኒያላ እና ኦሜድላ ከተጫወተ በኋላ በ2004 ወደ አሰልጣኝነት የገባ ሲሆን ከፋ ቡና ፣ ቡሌ ሆራ ፣ ሀድያ ሌሞ ፣ እንጅባራ ከተማ እና ዱራሜ ከተማን አሰልጥኗል። በዚህም በ2013 እንጅባራን በ2016 ደግሞ ዱራሜን ወደ ከፍተኛ ሊግ ያሳደገው አሰልጣኝ ባለፈው ዓመት በነበረበት ዱራሜ ከተማ ውሉን አራዝሟል።
ከዛ በተጨማሪ የ16 ነባር ተጫዋቾችን ውል አድሰው የ8 አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቁ ቅዱስ ደግፌ ከወልዲያ ግብ ጠባቂ ፣ ተስፋልዑል ከበደ ከአ.አ ዩኒቨርሲቲ ቀኝ ተከላካይ ፣ ታዬ ወርቁ ከሀምበርቾ የመሃል ተከላካይ ፣ ተመስገን አሰፋ ከሀምበርቾ አማካይ ፣ ሙጃይድ መሀመድ ከአሶሳ ከተማ አማካይ ፣ አቤል አስፋው ከሺንሺቾ አማካይ ፣ ወንድማገኝ ኢያሱ ከባቱ ከተማ አማካይ ፣ ኃይለኢየሱስ ዓለሙ ከሀምበርቾ አጥቂ ቡድኑን ተቀላቅለዋል።