ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ ቡድኑን በአዳዲስ ተጫዋቾች አዋቅሯል

በቅርቡ አሰልጣኝ መሐመድ ኑርንማን የቀጠረው ሀላባ ከተማ ወደ 17 የሚጠጉ አዳዲስ ተጫዋቾችን የስብስቡ አካል አድርጓል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ዘለግ ላለ ጊዜ እየተሳተፉ ከሚገኙ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሀላባ ከተማ በኢትዮጵያ ዋንጫ ድል ዓመቱን የጀመረ ሲሆን ለቀጣዩ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ “ለ” ተሳታፊነቱን አጠንክሮ ለመቅረብ እንዲረዳው አሰልጣኝ መሐመድ ኑርንማን መሾሙ የሚታወስ ሲሆን ወደ 17 አዳዲስ ተጫዋቾችን ደግሞ በአዲስ መልኩ ወደ ስብስቡ አካትቷል።

የቀድሞው የጅማ አባጅፋር ፣ መቐለ ፣ አዳማ እና መቻል የመሐል ተከላካይ አሚኑ ነስሩ ፤ በወልቂጤ ከተማ እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በሀድያ ሆሳዕና ያሳለፈው አጥቂው የኋላሸት ሠለሞን ፤ የቀድሞው የፋሲል ከነማ ፣ ወልዲያ እንዲሁም በኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጫወተው መጣባቸው ሙሉ ፤ በወልዋሎ ፣ መቻል እና ቤንች ማጂ ቡና ግብ ጠባቂ ሆኖ ያገለገለው ጃፈር ደሊል ፤ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና በኢትዮጵያ ቡና ከወጣት እስከ ዋናው ድረስ የተጫወተው አጥቂው ከድር ዓሊ ፤ በወላይታ ድቻ አማካይ ቦታ ላይ ሲጫወት የምናውቀው ፊንሐስ ተመስገንን ጨምሮ አብዱልቃድር ናስር አማካይ ከሻሸመኔ ፣ አቡበከር ካሚል ተከላካይ ከኤሌክትሪክ ፣ በክሪ መሐመድ ከንብ ተከላካይ ፣ እንዳሻው እሸቱ ግብ ጠባቂ ከወላይታ ድቻ ፣ በፍቃዱ ሕዝቅኤል አማካይ ከኤሌክትሪክ ፣ ማኑሄ ጌታቸው አጥቂ ከወሎ ኮምቦልቻ ፣ ቢላል ገመዳ አማካይ ከወሎ ኮምቦልቻ ፣ ዑስማን መሐመድ ተከላካይ ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ፣ ዘላለም አበበ አማካይ ከጅማ ፣ ዘመድኩን ሽሮ ተከላካይ ከይርጋጨፌ ቡና እና ሙሉቀን ተከላካይ ከኤሌክትሪክ የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች ናቸው።

ቡድኑ ውላቸው የተጠናቀቀ ነባር ተጫዋቾችን ውል ያደሰ ሲሆን አራት ወጣቶችን ደግሞ ከተስፋ ቡድኑ አሳድጓል።