የወቅቱ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው እና የረዳታቸውን ውል ለተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።
የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከመጀመሪያው ሽንፈት በኋላ በተከታታይ ባደረጓቸው የሊግ ጨዋታዎቻቸው ሦስቱንም በድል ተወጥተው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በዘጠኝ ነጥቦች መቀመጥ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት ኮንራታቸው ተገባዶ የነበሩትን የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ውል ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ስለማራዘማቸው ሶከር ኢትዮጵያ መረጃው ደርሷታል።
የቀድሞው የደቡብ ፓሊስ ፣ ሀዋሳ ፣ አዳማ ፣ ድሬዳዋ ፣ ሰበታ እና ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ሆነው ያገለገሉት አሰልጣኙ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ወደ ቀደመው ክለባቸው ሲዳማ ቡና በመመለስ በሊጉ እንዲቆይ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በያዝነው ዓመትም ቡድኑን እየመሩ ያሳዩት ውጤታማ የውድድር ጉዟቸውን የተመለከተው የክለቡ ቦርድ አሰልጣኙ በአንድ ዓመት ኮንትራት ከክለቡ ጋር እንዲቀጥሉ ባደረገው የጋራ ስምምነት በይፋ ውላቸው እንዲታደስ ተደርጓል።
በሌላ ዜናም የክለቡ ረዳት ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት የቀድሞው የሀዋሳ ፣ ወልቂጤ ፣ ደቡብ ፓሊስ እና ቡታጅራ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳም በክለቡ የውል ዘመናቸው መራዘሙንም ጭምር ዝግጅት ክፍላችን አውቃለች።