የአምስተኛው ሳምንት መገባደጃ የሆኑ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድሉን ያስመዘገበው ኤሌክትሪክ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ካስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና የሚያደርጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ባህር ዳር ከተማን አንድ ለባዶ በማሸነፍ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸውን ያስመዘገቡት ኤሌክትሪኮች ነጥባቸውን አምስት አድርሰዋል። ኤሌክትሪኮች እንደባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ጥብቅ መከላከል እና ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በተከተሉበት ጨዋታ ድል ከማድረጋቸው ባለፈ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረባቸውን ባለማስደፈር የመከላከል ጥንካሬያቸውን ዐሳይተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተለይም በሁለቱም የመጨረሻ መርሐግብሮች የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ እምብዛም ውጤታማ ያልነበረው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው በብዙ ረገድ ተሻሽሎ ቀርቧል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በነገው ጨዋታም የተለመደው አጨዋወታቸውን ይተገብራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ቡድናቸው የግብ ዕድሎችን በመጠቀም ረገድ የታዩበትን ክፍተቶች ማስተካከል እና የአፈፃፀም ብቃታቸውን ከፍ የማድረግ ሥራ ይጠበቅባቸዋል።
በሊጉ መክፈቻ መርሐግብር መቐለ 70 እንደርታን በማሸነፍ ዓመቱን ቢጀምሩም በባህር ዳር ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ። በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት በገጠማቸው የመጨረሻ መርሐግብር ላይ በሁሉም ረገድ ብልጫ ቢያሳዩም ከሽንፈት ያልዳኑት ነብሮቹ በጨዋታው የግብ ማስቆጠር ድክመታቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ከዚህ ቀደም የአጨዋወታቸው ዋነኛ መገለጫ የነበረው የመከላከል ጥንካሬ በዘንድሮ የውድድር ዓመት በውስን መልኩ ቀንሷል፤ ቡድኑ ሽንፈት ባስተናገደባቸው ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አራት ግቦች ማስተናገዱም የዚህ አንድ ማሳያ ነው። የነገውን ጨምሮ በቀጣይ የሊጉ ጨዋታዎችም የግብ ማስቆጠር ችግራቸውን ጨምሮ ካለወትሮ ተጋላጭ እየሆነ ያለው የመከላካል አደረጃጀታቸው ላይ ለውጦች ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሽመክት ጉግሳ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነቱም ቡድኖቹ እኩል አራት አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ወላይታ ድቻ ከ ስሑል ሽረ
እኩል ስድስት ነጥብ የሰበሰቡ ቡድኖችን የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ መዝጊያ መርሐግብር ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቅ ነው።
ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት የጦና ንቦቹ ተከታታይ ድሎች ለማስመዝገብ በውድድር ዓመቱ ሽንፈት ካልቀመሰው ስሑል ሽረ ጋር ይጫወታሉ። በመጀመርያዎቹ ሦስት መርሐግብሮች ዘጠኝ ግቦችን በማስተናገድ በመከላከሉ በኩል ደካማ አጀማመር ያደረገው ቡድኑ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ በአወንታ የሚነሳ እንቅስቃሴ በማድረግ ባለፉት ጨዋታዎች የታየው የመከላከል ድክመት ቀርፏል። በጨዋታው ወደ አጥቂዎች በሚሻገሩ ረዣዥም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረገው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ለተጋጣሚው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት የሚመጥን ዝግጅት እና አቀራረብ ይዞ መግባት ግድ ይለዋል።
አዳማ ከተማ ላይ በተቀዳጁት ድል ዓመቱን የጀመሩት ስሑል ሽረዎች በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞክር እና በፈጣን ሽግግሮች የግብ ዕድሎች የሚፈጥር ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ጠጣሩ የመከላከል አደረጃጀት ዋነኛው የቡድናቸው መገለጫ ነው። ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች በማስቆጠር ተስፋ ሰጪ አጀመማር ማድረግ ቢችልም የማጥቃት ጥንካሬው ከጨዋታ ጨዋታ መቀዛቀዞች ታይቶበታል። በነገው ዕለትም የመከላከል ጥንካሬውን ከማስቀጠል ባለፈ ባለፉት ጨዋታዎች አባካኝ የነበረው የፊት መስመራቸው የአፈፃፀም ድክመት መቅረፍ ይኖርባቸዋል።
ወላይታ ድቻዎች ከቅጣትም ሆነ ጉዳት ነጻ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ለጨዋታ ሲቀርቡ በስሑል ሽረ በኩል ግን ኬቨን አርጉዲ እና ዐወት በሪሁ ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው በነገው ጨዋታ አይሰለፉም።
የተሰረዘው እና በስሑል ሽረ የሁለት ለባዶ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር ሁለት ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ በሁለቱም ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ በጨዋታዎች እኩል አንድ አንድ ግብ አስቆጥረዋል።