የስድስተኛው ሳምንት የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገቡ ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ለመድን
ከተከታታይ በድል ካልታጀበ ጉዞ ለመላቀቅ በአንፃሩ ወልዋሎ ደግሞ ነፍስ የመዝራት የሚፋለሙበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ሽንፈት በማስተናገድ መጥፎ አጀማመር በማድረግ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎች በቀጣይ ስጋት ውስጥ ሊጥላቸው የሚችል ጉዞ ላይ ሲገኙ በሊጉ ምንም ነጥብ ያልሰበሰቡ ብቸኛ ክለብ አድርጓቸዋል።
በአራቱም ጨዋታዎች ዝቅተኛ የውህደት ደረጃ ላይ ያለ፣ የግል ስህተቶች የሚበዙበት እና የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገር የታየው ወልዋሎ
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች ማድረግ ግድ ይለዋል።በቀዳሚነት ግን በኋላ ክፍል ያለው የቡድኑ አደረጃጀት ባለፉት ጨዋታዎች ካሳየው ደካማ እንቅስቃሴ አንፃር በብዙ መስተካከል የሚኖርበት ነው። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ በመከላከሉ ላይ ያለው ጉልህ ድክመት ባለፉት ጨዋታዎች እጅ እንዲሰጥ ምክንያት ሲሆነው ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪም ኪሩቤል ወንድሙ ካስቆጠራት ግብ ውጭ ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው ቡድኑ በነገው ጨዋታ በአራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የኋላ ክፍል ያለው መድን እንደመግጠሙ ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀው ፈተና ቀላል አይሆንም።
ከአራት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦች የሰበሰቡት ኢትዮጵያ መድኖች ነጥብ ተጋርተው በወጡባቸው ሦስት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር አልቻሉም።
መድኖች ነገም እንደባለፉት ጨዋታዎች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ካሳዩ እና ዕድሎች ከፈጠሩ ከወልዋሎ የመከላከል ድክመት ጋር ተዳምሮ በፊት መስመሩ ላይ መሻሻል እንድንጠብቅ የሚያደርገን ጉዳይ ቢሆንም የፊት ጥምረቱ ግቦችን የማስቆጠር ድክመት ግን የቡድኑ ዋነኛ ደካማ ጎን ነው። ቡድኑ በተሸነፈበት የመጨረሻው ጨዋታ ጨምሮ በሊጋችን ደረጃ አንፃር ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች መፍጠር መቀጠሉ እንደ አውንታ የምናነሳለት ጥሩ ጎን ቢሆንም ዕድሎችን የመጠቀም ድክመቱ የቡድኑ እንቅስቃሴ በውጤት እንዳይታጀብ አድርጎታል።
በውድድር ዓመቱ ከሌላው ጊዜ በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የሚይዝ አቀራረብ ይዘው የቀረቡት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በነገው ጨዋታም የአጨዋወት ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም ሆኖም ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው የማጥቃት ጥምረት ላይ ውስን ለውጦች የሚያደርጉበት ዕድል እንዳለ ይታመናል።
በጉዳት እና ቅጣት እየታመሱ ለሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች መልካሙ ዜና የመሀል ተከላካዩ ሚልዮን ሰለሞን ከቅጣት ሲመለስ አጥቂው መሀመድ አበራም ከጉዳቱ አገግሟል።በወልዋሎ በኩል ነጋሲ ገብረእየሱስ፣ ሔኖክ ገብረእግዚአብሄር፣ ስምዖን ማሩ እና ስምዖን ተኽለ አሁንም ጉዳት ላይ በመሆናቸው በነገው ጨዋታ አይሰለፉም።
ሁለቱም ቡድኖች በነገው ዕለት በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።
ፋሲል ከነማ ከ አርባምንጭ ከተማ
ዐፄዎቹ እና አዞዎቹ የሚያደርጉት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል
በሊጉ የመጀመርያ ጨዋታ ድል ካስመዘገቡ ወዲህ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ የተጋሩት ዐፄዎቹ ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስን እና ነጥባቸው ማሳደግን እያለሙ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ከባለፉት ጨዋታዎች የተሻለ ብቃት ያሳዩት ዐፄዎቹ ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር ነጥብ ተጋርተው መውጣታቸው ለክፉ የሚሰጥ ውጤት ባይሆንም የነገው መርሃግብር ነጥብ በተጋሩባቸው ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች ሦስቱን ብቻ አሳክተው የሚጀምሩት ጨዋታ እንደመሆኑ በቀጣይ ጫና ውስጥ ላለመግባት ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች መላቀቅ ግድ ይላቸዋል።
የዐፄዎቹ የተከላካይ ክፍል ካለፉት አምስት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር የወጣበት አጋጣሚ አንድ ብቻ ቢሆንም ጥንካሬው ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። በነገው ጨዋታ ግን
ከተጋጣሚ የአጨዋወት ምርጫ አንፃር የአርባምንጭ ከተማ ቀጥተኛ አቀራረብ ለቡድኑ የስጋት ነጥብ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በመጨረሻው ጨዋታ ከተከላካዮች ጀርባ የሚፈጠረው ሰፊ ክፍት ቦታ የመሸፈን ውስን ክፍተቶች የታየበት ቡድኑ ተሻጋሪ ኳሶች የሚያቋርጥበትን መንገድ ማጤን የግድ ይለዋል።
በነገው ዕለትም እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቀው አህመድ ሁሴንን የያዘ ቡድን እንደመግጠማቸው የቅብብል ስህተቶች መቀነስ እና ከተከላካይ ጀርባ የሚፈጠሩ ክፍተቶች በተሻለ መንገድ መሸፈን ይጠበቅባቸዋል።
ሁለት ሽንፈት፣ አንድ አቻ እና አንድ ድል በማስመዝገብ አራት ነጥቦች የሰበሰቡት አዞዎቹ ከውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ድላቸው መልስ ተከታታይ ሦስት ነጥቦች ለማግኘት ፋሲል ከነማን ይገጥማሉ። ባህርዳር ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ጨምሮ በዋነኝነት በረጃጅም ኳሶች እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ የሚሞክሩት አዞዎቹ በመጨረሻው ጨዋታ ውጤት ያስገኘላቸው የተጫዋቾች ምርጫ በነገው ዕለትም ይቀጥላል ተብሎ ሲገመት በሌላ በኩል ተገማች የሆነው የማጥቃት አጨዋወት ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በአርባምንጭ ከተማ በኩል አበበ ጥላሁን ቅጣቱን ጨርሶ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን ሳሙኤል አስፈሪ በጉዳት አይሰለፍም ከዚ በተጨማሪም አሸናፊ ፊዳ ለነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። በዐፄዎቹ በኩል ከሰባት ወራቶች ጉዳት የተመለሰው አማኑኤል ገብረሚካኤል ልምምድ ቢጀምርም ለነገው ጨዋታ አይደርስም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪምየር ሊግ በስምንት አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን ፋሲል ከነማ በሦስት አጋጣሚዎች እንዲሁም አርባምንጭ ከተማዎች በአንድ አጋጣሚ ሲያሸንፉ የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው። በጨዋታዎቹ ዐጼዎቹ 7 አዞዎቹ ደግሞ 4 ግቦች አስቆጥረዋል።