ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ከሊጉ መሪ ጋር በነጥብ ተስተካክለዋል

ወላይታ ድቻ በካርሎስ ዳምጠው ብቸኛ ግብ ሀድያ ሆሳዕናን 1ለ0 በመርታት ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ ከሊጉ መሪ ጋር በነጥብ መስተካከል ችለዋል።


በመጨረሻ የሊግ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቁበት ወቅት ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሠመረ ሀፍታይን በበየነ ባንጃው የተኩበት ብቸኛ ለውጣቸው ሲሆን ወላይታ ድቻዎች ግን ስሑል ሽረን 1ለ0 የረታው ስብስባቸው ላይ ምንም ቅያሪ ሳያደርጉ ቀርበዋል።

ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የምሽቱ መርሃግብር የመጀመሪያው አጋማሽ አሰልቺ ገፅታ የተላበሰ ነበር። ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረቦች እንዲሁም ጥራት ያላቸው ዕድሎች ተፈጥረው ማየትን ባስናፈቀን አጋማሽ ምንአልባትም 22ኛው ደቂቃ ወላይታ ድቻዎች በያሬድ ዳርዛ አማካኝነት ከግራ ይዘው ወደ ሳጥን የገቡትን ኳስ በተጫዋቹ ላይ ዳግም ንጉሴ ጥፋት ሰርቶ የነበረ ቢሆንም የዕለቱ ዋና ዳኛ መለሠ ንጉሴ የፍፁም ቅጣት ምት አያሰጥም በሚል ሳይሰጡ የቀሯት አጋጣሚ በአጋማሹ በልዩነት ጎልታ ልትነሳ የምትችለዋ ክስተት ነበረች ማለት ይቻላል።

በተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ መጓዙን የቀጠለው ጨዋታ 27ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛውን ሙከራ አስመልክቶናል ፤ ብሩክ በየነ ከተከላካይ ጀርባ በግንባር ተጨራርፎ የደረሰውን ኳስ ወደፊት ገፍቶ ከሳጥኑ አጠገብ መቶ ቢኒያም ገነቱ ካወጣበት በኋላ የቀሩት ደቂቃዎች አንድም የረባ ነገር ሳያስመለክቱን ተገባዷል።

ብዙም የተሻሻሉ እንቅስቃሴዎች ያልነበሩት ነገር ግን ከመጀመሪያው አኳያ ጥቂት ቅርፅ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ኳስን በመቆጣጠር በሽግግር ለመጫወት ጥረት ያደርጉ የነበሩት የጦና ንቦቹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በመድረስ ጥቃት ለመሰንዘር የሚያደርጉት ጥረት ግን የተሻለ ነበር።

56ኛው ደቂቃ በጥሩ ሁኔታ ከያሬድ ዳርዛ ያገኘውን ኳስ አብነት ደምሴ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት አክርሮ መቶ ያሬድ በቀለ በጥሩ ቅልጥፍና ያመከናት ኳስ ወላይታ ድቻዎች በአጋማሹ የፈጠሯት ቀዳሚዋ ሙከራ ሆናለች። ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ሲጥሩ በተደጋጋሚ ሲቸገሩ የተመለከትናቸው ነብሮቹ መስመር ላይ መዳረሻቸውን ያደረጉ ረዘም ያሉ ኳሶችን በተጠቀሙበት ወቅት 64ኛው ደቂቃ ከግራ የተነሳው ፀጋአብ ግዛው የግል አቅሙን ተጠቅሞ በጥልቀት ከሳጥን ጠርዝ የመታት ኳስን ቢኒያም ገነቱ በጥሩ ዕይታ አድኖበታል።

ጨዋታው ቀጥሎ 67ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ በፈጣን ሽግግር መሳይ ሠለሞን ከቀኝ መስመር የተጣለውን ኳስ ወደ ሳጥን ሲያሻማ የግብ ዘቡ ያሬድ በቀለ የጨረፋትን ኳስ ከጀርባው የተገኘው ካርሎስ ዳምጠው መረቡ ላይ በማሳረፍ ወላይታ ድቻን መሪ አድርጓል።

ጎልን ካስተናገዱ በኋላ በይበልጥ ማጥቃቱ ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ተስበው መንቀሳቀስ የቻሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች የተጋጣሚያቸውን የጥንቃቄ አጨዋወት በትዕግስት ማስከፈቱ ላይ ግን ስኬታማ አልነበሩም።

ካርሎስ ዳምጠው ካደረጋት እና ያሬድ በቀለ ከያዘበት የ82ኛ ደቂቃ  ሙከራ በስተቀር መከላከሉ ላይ ያመዘኑት ወላይታ ድቻዎች አጥራቸው አስጠብቀው ጨዋታውን 1ለ0 አሸንፈው ወጥተዋል። ውጤቱም ለቡድኑ ሦስተኛ ተከታታይ ሆኖ ሲመዘገብላቸው ከመሪው ሲዳማ ቡና ጋር ደግሞ በነጥብ ተስተካክለዋል።