መረጃዎች | 23ኛ የጨዋታ ቀን

የ6ኛው ሳምንት 3ኛ የጨዋታ ቀን መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

መቻል ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ባለፈው የውድድር ዓመት እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ለዋንጫ የተፎካከሩት መቻል እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚያገናኘው የሳምንቱ ታላቅ መርሃግብር በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂ ነው።

ከሲዳማ ቡናው ሽንፈት ወዲህ ሦስት ጨዋታዎች አከናውነው በሁለቱ ድል በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተው በመውጣት ሰባት ነጥቦች የሰበሰቡት መቻሎች ወልዋሎን ሦስት ለባዶ ባሸነፉበት የመጨረሻው መርሃግብር እጅግ የተሻሻለን ብቃት አሳይተዋል። ቡድኑ በጨዋታው በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ግቡን ሳያስደፍር ከመውጣቱም በላይ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያሳየው ጉልህ መሻሻል የፊት መስመሩ ጥንካሬ አጎልብቶታል። ጦሩ ምንም እንኳን በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች የሚያስቆጥር የፊት ጥምረት ቢኖረውም የአፈፃፀም ችግሩ ጨርሶ ቀርፎታል ለማለት አያስደፍርም። ቡድኑ ያስቆጠራቸው ግቦች ከሚፈጥራቸው የግብ ዕድሎች ብዛት አንፃር ሲታይ ጥቂት ነው፤ ወልዋሎን ያሸነፈበት የመጨረሻው መርሃግብርም የዚህ አንድ ማሳያ ነው። በነገው ዕለትም ከባለፉት ተጋጣሚዎች በጥንካሬ ረገድ የተሻለ የኋላ ክፍል ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው የአጨራረስ ብቃታቸው ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሦስት ጨዋታዎች አከናውነው አንድ አንድ ድል፣ አንድ ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት በመደዳ በማስመዝገብ አራት ነጥቦች የሰበሰቡት ሻምፕዮኖቹ ከሁለት መርሃግብሮች በኋላ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከጦሩ ጋር ይፋለማሉ።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባከናወኑት ጨዋታ በፍፁም ጥላሁን የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ሽንፈት ያስተናገዱት ንግድ ባንኮች ከፋሲል ከነማ ጋር በተካሄደው ጨዋታ በተራቸው በተስፋዬ ታምራት የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ቡድኑ በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችልም በፊት መስመር የነበራቸው የአፈፃፀም እንዲሁም የተጫዋቾች የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ከአንድ ግብ በላይ እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል። ንግድ ባንኮች ከኳስ ቁጥጥር በዘለለ የግብ ዕድሎች መፍጠር መቀጠላቸው በአውንታነቱ የሚነሳላቸው ጉዳይ ቢሆንም የፊት መስመር ጥምረቱ በቀደመው ጥንካሬው አይገኝም። ንግድ ባንኮች ከነገው ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች እያስቆጠረ የዘለቀውን የጦሩ የፊት መስመር እንቅስቃሴ መግታትም ሌላው የቤት ስራቸው ነው። 

በመቻል በኩል ነስረዲን ኃይሉ በጉዳት ሽመልስ በቀለ ደግሞ በቅጣት የማይኖሩ ሲሆን የአስቻለው ታመነ መሰለፍ ደግሞ አጠራጣሪ ነው። በአንጻሩ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ከጉዳት ተመልሷል። በንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ኤፍሬም ታምራት በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ27 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቻል 9 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ባንክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 13 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 37 ሲያስቆጥር ባንክ 31 አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ

ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች የተሸነፉት ቡናማዎቹ እና ተከታታይ ድልን እያለሙ የሚገቡት ምዓም አናብስት የሚያደርጉት የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር ነው።

በመጀመርያው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተው በሁለተኛው ደግሞ ድል በማስመዝገብ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት ቡናማዎቹ ከሽንፈት ለመውጣት መቐለ 70 እንደርታን ይገጥማሉ።

ቡናማዎቹ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ከማስመዝገባቸው በተጨማሪ በመርሃግብሮቹ አንድ ግብ ብቻ በማስተናገድ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ አጀማመር ቢያደርጉም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የመከላከል ክፍላቸው ተዳክሞ አራት ግቦች ለማስተናገድ ተገደዋል። በነገው ጨዋታም የማጥቃት ክፍላቸው ላይ ጥሩ መሻሻሎች ያሳዩት እና ድሬዳዋ ከተማ ላይ ሦስት ግቦች ያስቆጠሩትን መቐለዎች እንደ መግጠማቸው የኋላ ክፍላቸው ላይ የታዩትን ክፍተቶች መድፈን ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሲዳማ ቡና በተሸነፉበት ጨዋታ ላይ ጥቂት የማይባሉ ለአደጋ የሚያጋልጡ የቅብብል ስህተቶችን የፈጠሩት ቡናዎች በነገው ጨዋታ በተለይም በምስረታ ወቅት የሚፈጠሩትን የቅብብል ስህተቶች መቀነስ ግድ ይላቸዋል።  ተጋጣሚያቸው መቐለ 70 እንደርታ በመጨረሻው ጨዋታ ከኳስ ውጭ በተሻለ መንገድ ተጭኖ በመጫወት ውጤታማ የሆነ ቡድን መሆኑም ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።

ድሬዳዋ ከተማ ላይ የውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድል በማስመዝገብ ነጥባቸው ስምንት ያደረሱት ምዓም አናብስት ከመክፈቻው ሽንፈት በማገገም በተከታታይ ነጥብ ማስመዝገባቸው ቡድኑ በጥሩ መሻሻል እንዳለ ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ ያሳየው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥራት የፊት መስመሩን ጥንካሬ አጎልብቶታል።

በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸውን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸውን ተከትሎ መጠነኛ እፎይታ ያገኙት አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ አሁንም የመሀል ተከላካዮቹ ዮናስ ግርማይ እና መናፍ ዓወል በጉዳት፤ በጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ጋናዊ ተከላካይ ሸሪፍ መሐመድ ደግሞ በቅጣት ማጣታቸው የተከላካይ ክፍሉ ክፉኛ አሳስቶታል። በነገው ጨዋታው አማካዩ ቤንጃሚን አፉቱ ኮቴ በመሀል ተከላካይነት ያሰልፋሉ ተብሎ ሲጠበቅ በአማካይ ክፍሉ ከሚያድርጉት የተጫዋች ለውጥ ውጭ በአጨዋወትም ሆነ በተጫዋቾች ምርጫ ላይ በአሸናፊው ቡድን ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ አይገመትም። በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረውና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው አጥቂው ያሬድ ብርሀኑም በነገው ጨዋታ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል በፍቃዱ ዓለማየሁ እና መላኩ አየለ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ደግሞ ዮናስ ግርማይ እና መናፍ ዓወል በጉዳት፤ ሸሪፍ መሐመድ ደግሞ በቅጣት ምክንያት አይሰለፉም።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም አራት ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 3፣ መቐለ 2 አስቆጥረዋል። (በ2012 በኮቪድ ምክንያት የተሰረዘውና 1-1 የተጠናቀቀው ጨዋታን አያካትትም)