የአብዱልከሪም ወርቁ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ግብ መቻልን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስገኝታለች።
መቻል ወልዋሎን ካሸነፈው ቋሚ ውብሸት ጭላሎ፣ ግሩም ሐጎስ እና አቤል ነጋሽን በአልዌንዚ ናፍያን፣ ዓለምብርሃን ይግዛው እና የሐንስ መንግስቱ ተክተው ሲገቡ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ከፋሲል ጋር ነጥብ ከተጋራው ቋሚ ሲሞን ፒተር እና ቢንያም ካሳሁንን አስወጥቶ በፉዓድ ፈረጃ እና ሱሌይማን ሐሚድ ተክተው ገብተዋል።
ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ያላቸውን የቅርብ ተቃናቃኞች ያገናኘው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ተቀራራቢ ፉክክር እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በአጋማሹም ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ግን ንግድ ባንኮች የተሻሉ ነበሩ። በአመዛኙ በቀኝ መስመር ጥቃቶች ለመሰንዘር ጥረት ያደረጉት ንግድ ባንኮች ከአብዱልከሪም መሐመድ ተሻግረው አዲስ ግደይ እና ኪቲካ ጅማ ባደረጓቸው ሙከራዎች ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎችም ፉዓድ ፈረጃ ከማዕዝን ምት አሻምቷት ሱሌይማን ሐሚድ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳናት ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የፉክክር መንፈስ የተንፀባረቀበት ሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። ከመጀመርያው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት መቻሎች ወደ ጎል በመድረስም የተሻሉ ነበሩ፤ በተለይም ዓለምብርሃን ይግዛው አሻምቷት በነፃ አቋቋም የነበረው አብዱ ሙተላቡ በግንባሩ የሞከራት ሙከራ ጦሩን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። በሰባ ዘጠነኛው ደቂቃም በረከት ደስታ ከመሀል ሜዳ በጥሩ መንገድ ያሾለካትን ኳስ አብዱልከሪም ወርቁ አግኝቶ ግብ ጠባቂውን ጭምር በማታለል ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ በውስን መልኩ የተቀዛቀዘ የማጥቃት ክፍል የነበራቸው ንግድ ባንኮችም በባሲሩ ኡማር እና ሲሞን ፒተር አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በመቻል የአንድ ለባዶ አሸናፊነት ተጠናቋል።