ሳቢ በነበረው የምሽት ጨዋታ ቡናማዎቹ በአንተነህ ተፈራ ጎሎች ምዓም አናብስትን 2ለ0 አሸንፈው ወደ ድል ተመልሰዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ከሲዳማ ቡና ጋር ሽንፈት ካስተናገዱበት ከአምስተኛ ሳምንት ቋሚ አሰላለፍ ገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ኤርሚያስ ሹምበዛ እና ኮንኮኒ ሃፍዝን አስወጥተው ራምኬል ጀምስ ፣ ኦካይ ጁል እና ዳዊት ሽፈራውን ሲያስገቡ መቐለ 70 እንደርታዎች ድሬዳዋ ከተማን ካሸነፉበት ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ሸሪፍ መሐመድን በሄኖክ አንጃው ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ምሽት 1 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ሙሉቀን ያረጋል መሪነት የተጀመረው እና ሳቢ የነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ያስመለከተ ቢሆንም ቡድኖቹ ግብ ለማሰቆጠር የተቃረበ ሙከራ ሲያደርጉ አልተስተዋሉም። ምናልባትም በአጋማሹ ከባድ የሚባለውን ሙከራ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ16ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጉ ሲሆን ርቀት ላይ ሆነው የሞከሩትን ጠንከር ያለ ሙከራ የመቐለ 70 እንደርታው ግብ ጠባቂ ሶፎንያስ ሰይፈ በግሩም ሁኔታ መልሶባቸዋል።
ማራኪ የኳስ ቅብብል እና እንቅስቃሴ ባስመለከቱት በመጀመሪያዎቹ ሃያ አምስት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት ነበር። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ቡና ግብ የማስቆጠር ሙከራ በማድረግ የተሻለ ተንቀሳቅሷል። በአጠቃላይ አጋማሹ በአጫጭር የኳስ ቅብብል ጋር የታጀበ እና ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግር ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ለመግባት ጥረት ያደረጉበት እና በመልሶ ማጥቃት ቶሎ ቶሎ ወደ ሦሰተኛው የሜዳ ክፍል መድረስ የቻሉበት ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡናዎች ጫና ፈጥረው ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ በአጫጭር ኳስ ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል ሲደርሱ ተስተውለዋል። በ47ኛው ደቂቃ ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ርቀት ላይ በተገኘ ኳስ አደገኛ ሙከራ አድርገው የመቐለው ግብ ጠባቂ ወደ ውጪ አውጥቶባቸዋል። ምዓም አናብስቶች በአንፃሩ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶባቸው ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ አድርገዋል።
የተሻለ የጨዋታ የበላይነት ከግብ ማግባት ሙከራ ጋር ያሳዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ 70 ተከላካዮች ባደረጉት በእጅ ንክኪ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ፍፁም ቅጣት ምቱን አንተነህ ተፈራ አስቆጥሮ መሪ መሆን ችለዋል። መቐለ 70 እንደርታዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማግባት ወደ ፊት ሄደው ግብ ለማግባት ሙከራ በሚያደርጉበት ቅፅበት በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። በ58ኛው ደቂቃ ላይ መቐለ 70 እንደርታዎች ባደረጉት ሙከራ በመልስ ምት የተሻማውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ዳዊት ሽፈራው በግሩም ሁኔታ የመቐለን ተከላካዮች አታሎ በማለፍ ያሻገረውን ኳስ አንተነህ ተፈራ አግኝቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ሽንፈት ላለመቀበል ወደ ጨዋታ ለመመለስ በተደጋጋሚ የተጫዋች ቅያሪ ያደረጉት ምዓም አናብስቶች በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ወደ ፊት ተጠግተው ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ከሸንፈት የተመለሱት የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ነጥቡን አስጠብቀው ለመውጣት ጠንከር ያለ መከላከል አድርገው ሙከራዎቻቸውን ተረባርበው አበላሽተውባቸዋል። በዚህም ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።