መረጃዎች | 24ኛ የጨዋታ ቀን

የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ የሆኑ ሁለት መርሐግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ!

ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ከሽንፈት፤ አዳማ ከተማ ደግሞ ከድል መልስ የሚያደርጉት ጨዋታ ከሁለቱም ቡድኖች አቀራረብ በመንተራስ በጥሩ እንቅስቃሴ የታጀበ ጨዋታ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።

ተከታታይ የሁለት ሳምንት ጨዋታዎችን በድል ከተወጡ በኋላ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች አንድ አቻ እና አንድ ሽንፈት የገጠማቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በመቐለ ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም እያለሙ ነገ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይታመናል። ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻው ጨዋታም ግቦችን ማስቆጠራቸውን ቢቀጥሉም በኋላ ክፍሉ
ላይ የነበረው ጉልህ ድክመት ሦስት ግቦች አስተናግደው እንዲሸነፉ ዋነኛ ምክንያት ነበር። ቡድኑ የቅብብል ስህተቶቹ እና ያልተመጠነው የተከላካዮች የመጨረሻ መስመር ጎሎች በቀላሉ እንዲቆጠሩበት ያደረገ ሲሆን በፊት መስመሩ ላይ የነበረውን ጥንካሬ ይዞ መቀጠሉ ግን በነገው ጨዋታም ግምት እንዲሰጠው ያደርጋል። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በነገው ዕለት ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎች ያሳየው እና እና በፈጣን አጥቂዎች የሚመራውን የቀድሞ ክለቡ አዳማ ከተማን እንደመግጠሙ የባለፈው ሳምንት ጨዋታ ስህተቶችን ላለመድገም በተለይም በኋላ ክፍሉ  በይበልጥ ጥንቃቄ መርጦ እንደሚገባ መገመት ይቻላል።

በስሑል ሽረ የመክፈቻ ጨዋታን ከተሸነፉ በኋላ በቀጣዮቹ ተከታታይ ሦስት መርሐግብሮች ሽንፈት ያልቀመሡት አዳማ ከተማዎች በቀድሞው አሰልጣኛቸው ከሚሰለጥነው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ከቆሙበት ድላቸው ለመቀጠል ብርቱ ፉክክርን ያስተናግዳሉ። ባደረጓቸው ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ አንድ አቻ እና ሁለት ድል ያስመዘገቡት አዳማ ከተማዎች በአምስተኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን 2ለ0 በረቱበት ወቅት ይዘውት የገቡትን የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመያዝ የሚጥር አቀራረብ ነገም በተመሳሳይ  ያስቀጥላሉ ተብሎ ይታመናል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ተመሳሳይ አጨዋወት ምርጫው ያደረገ እና ጠንካራ የአማካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደመሆኑ የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ ነው። ቡድኑ ከዚህ በተጨማሪም በአማካይ ክፍሉ ላይ የሚታይበትን የፈጠራ እጥረት መቅረፍ ግድ ይለዋል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት በመጨረሻው ጨዋታ ያልተሳተፈው መስዑድ መሐመድ ከጉዳቱ አገግሞ ለጨዋታ ዝግጁ ሲሆን የአጥቂው ቻርለስ ሙሴጌ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ነው። በአዳማ ከተማ በኩል የግብ ዘቡ ዳግም ተፈራ በጉዳት የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን አማካዩ አድናን ረሻድ ግን ከአንድ ጨዋታ ቅጣቱ ተመልሷል።

ረዘም ያለ የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ በሊጉ 24 ጊዜ ሲገናኙ አዳማ ከተማዎች 12 ጊዜ ባለድል በመሆን የበላይ ሲሆኑ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ በ6 ይከተላሉ የተቀሩት 6 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተቋጩ ነበሩ። በጨዋታዎቹ አዳማዎች 28 ሲያስቆጥሩ ድሬዎች በአንጻሩ 20 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ረዘም ያለ የግንኙነት ታሪክ ያላቸውን ክለቦች የሚያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ መርሐግብር ምሽት 1 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በአዳማ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው ሀዋሳ ከተማዎች ከሚታይባቸው የውጤት መዋዠቅ ወጥተው በወጥነት ለመቀጠል የነገውን ድል አጥብቀው ይፈልጉታል። ሲዳማ ቡናን በደርቢው የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ላይ በረቱበት ወቅት በመከላከሉ ላይ ጠጣር እንደነበር አሳይቶን የነበረው ቡድኑ በቀጣዮቹ ጨዋታዎች ላይ ግን በቀላሉ ተጋላጭ እየሆነ መጥቷል። የኋላ ክፍሉ ድክመትም በነገው ዕለት ጨምሮ በወጥነት መቅረፍ የሚገባው ትልቁ የቤት ሥራው ነው። ዓሊ ሱሌይማንን ትኩረት ባደረጉ ቀጥተኛ አልያም ፈጣን ሽግግሮች ለማጥቃት የሚሞክረው ቡድኑ በመከላከሉ ጠንካራ የሆነውን ኤሌክትሪክ እንደመግጠሙ ፈተናው ቀላል እንደማይሆንለት መገመት ይቻላል።

ከመጀመርያው ጨዋታ ሽንፈት ወዲህ ሦስት አቻ እና አንድ ድል ያስመዘገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን ለማስመዝገብ ከሐይቆቹ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።

ከቅርብ ሳምንታት ብቃቱ ወረድ ያለ ብቃት ባሳየበት ጨዋታ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ጎል አልባ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ የመከላከል ጥንካሬውን ማስቀጠሉ ትልቁ ስኬቱ ቢሆንም የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱ ግን አመርቂ ነው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። ቡድኑ በነገው ዕለትም የተለመደው ጠጣር፣ ለተጋጣሚ ሰፊ የመጫወቻ ቦታ ሰጥቶ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች የሚፈጥረውን አጨዋወት ይተገብራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በማጥቃቱ ላይ የሚስተዋልበትን ውስንነት መቅረፍ ዋነኛው የቤት ሥራቸው ነው።

በሀዋሳ ከተማም ሆነ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ጉዳትም ሆነ ቅጣት ሳይኖር ለጨዋታው የሚገናኙ ይሆናል።

በ42 ግንኙነቶች ኤሌክትሪክ 17 ሲያሸንፍ ሀዋሳ 15 አሸንፏል። 10 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ኤሌክትሪክ 63 ፣ ሀዋሳ ደግሞ 48 ጎሎችን አስቆጥረዋል።