የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ያለበትን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርግበት ቦታ ታውቋል።
በ2025 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ በማጣሪያው ከኮንጎ ዲ.ሪ ፣ ጊኒ እና ታንዛኒያ ጋር በምድብ 8 ተደልድሎ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አሳክቶ 1 አስቆጥሮ 9 ጎሎች የተቆጠሩበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ ግርጌ ላይ የተቀመጠ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም የምድብ 5ኛ እና 6ኛ ጨዋታውን የፊታችን ሕዳር 7 ከታንዛኒያ እና ሕዳር 10 ደግሞ ከኮንጎ ዲ.ሪ ጋር የሚያደርግ ሲሆን የመጀመሪያውን በሜዳው ሊያደርገው የነበረውን ጨዋታ የካፍ ፍቃድ ያለው ስታዲየም ባለመኖሩ የት ሊያደርግ እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ደርሷታል።
በዚህም ዋልያዎቹ ሕዳር 10 ቀን ከኮንጎ ዲ.ሪ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ ማቅናታቸው የማይቀር ስለሆነ የመጀመሪያውን የሕዳር 7 የታንዛኒያ ጨዋታም እዛው ለማድረግ መወሰናቸው ተረጋግጧል።