አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የዩጋንዳውን የሴቶች ክለብ ለማሰልጠን ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን የሴካፋ ሻምፒዮን ያደረጉት አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል በጥር ወር መጨረሻ ለአራት ዓመታት ካገለገሉበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ያለ ስራ የቆዩ ሲሆን በመጨረሻም ወደ ዩጋንዳ ማምራታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
አሠልጣኝ ፍሬውን ለማስፈረም የተስማማው ካምፓላ ኩዊንስ የሴቶች ክለብ ነው። የፉፋን የሱፐር ሊግ ውድድር አንድ ጊዜ ማሸነፍ የቻለው ካምፓላ ኩዊንስ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በቻርለስ አይኮህ እየተመራ ቢጀምርም ከ5 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚጠበቅበት 15 ነጥቦች ዘጠኙን ብቻ በማሳካቱ እና በኩዋምፔ ሙስሊም ሌዲስ በ4 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን መሪነት በመበለጡ የክለቡ አመራሮች የአሰልጣኝ ለውጥ ለማድረግ ወስነዋል። በዚህም ኢትዮጵያዊው አሠልጣኝ ፍሬው ቡድኑን እንዲመራ መወሰናቸው ታውቋል። አሠልጣኙም ፊርማውን ለማጠናቀቅ ይህንን ዘገባ ባጠናከርንበር ሰዓት ዩጋንዳ ካምፓላ እንደገባ አውቀናል።
የአሰልጣኝ ፍሬው ረዳት በመሆን የቀድሞ የኪታራ ክለብ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ሻሮን ኪዛ እና የቀድሞ የዩ ሲ ዩ ተጫዋች የነበረችው ካርዲናልስ መሾማቸውን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።