መረጃዎች | 26ኛ የጨዋታ ቀን

በ7ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የሚከናወኑ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርቧል።

መቻል ከ አዳማ ከተማ

አራት ሽንፈት አልባ ሳምንታት ያሳለፉና በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በመጨረሻው ሳምንት ሻምፕዮኖቹን አንድ ለባዶ በመርታት ወሳኝ ድል ያስመዘገቡት መቻሎች ሁለት ተከታታይ ድል ከማስመዝገብም በዘለለ መሻሻሎች አሳይተዋል።

ቡድኑ ተጠባቂ በነበረው የመጨረሻው መርሃግብር በተከላካይ ክፍሉ የነበረው መረጋጋትም በቅርብ ሳምንታት በይበልጥ ያጎለበተው አወንታዊ ጎን ነው። ጦሩ በመጀመርያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች ቢያስተናግድም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን መረቡን ባለማስደፈር ጉልህ መሻሻሎች አሳይቷል። 

ሆኖም በነገው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገረውን ጥሩ የፊት መስመር ጥምረት ያለው አዳማ ከተማ መግጠማቸውን ተከትሎ የባለፉት ሳምንታት ጥንካሬያቸው ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት መርሃግብሮች በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ተሳትፎ የነበራቸው ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች በነገው ጨዋታ አበርክቷቸው የሚገደብበት ዕድል የሰፋ ነው።

በመጀመርያው ጨዋታ በስሑል ሽረ ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ካከናወኗቸው አራት ጨዋታዎች በእኩሌታ ሁለት ድልና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት አዳማዎች የዓመቱ ሦስተኛ ድላቸው ለማስመዝገብ ጦሩን ይገጥማሉ።

ብዙዎች ከሊጉ መጀመር አስቀድሞ የገመቱት ግምት በመፋለስ መልካም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በአምስት ጨዋታዎች የሰበሰቧቸው ስምንት ነጥቦች ከገጠሟቸው ቡድኖች ጥንካሬ አንፃር ሲታይ መልካም የሚባል ነው።

በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ አብዲ ቡሊ ለነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ ባለፈው ጨዋታ አባካኝ የነበረው የፊት መስመራቸው ዕድሎችን የመጠቀም አቅም ማስተካከል ቀዳሚው ስራቸው ነው። ተጋጣሚያቸው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረና የተረጋጋ መሆኑም ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም። 

ከዚህ በተጨማሪ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ቡድኑ የመስመር ጥቃቶች ለማቆም ሲቸገር መታየቱ ከጦሩ የጨዋታ ዕቅድ መነሻነት በነገው ጨዋታ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ሌላው ጉዳት ነው።
                                              
ከወገብ በላይ ባለው የሰንጠረዡ ክፍል ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ቡድኖች የሚያገናኘው የነገው ጨዋታ አሸናፊውን ወደ መሪዎቹ የማስጠጋት አጋጣሚን ይዞ የሚመጣ እንደመሆኑ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎም ይገመታል።

በመቻል በኩል ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች በቅጣት ምክንያት ያልተሰለፈው አምበሉ ሽመልስ በቀለ ቅጣቱ ባለማጠናቀቁ አይሰለፍም። በአዳማ ከተማ በኩል የዳግም ተፈራ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።

መቻል እና አዳማ በሊጉ 33 ጨዋታቸውን አከናውነዋል፤ በግንኙነቱ ሁለቱም ቡድኖች እኩል 10 10 ጊዜ አሸንፈዋል፤ የተቀሩት 13 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተገባደዱ ናቸው።
በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ 55 ግቦች ውስጥ አዳማ 28 መቻል ደግሞ 27 ግቦችን አስመዝግበዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ መቐለ 70 እንደርታ

በሁለት ነጥቦች የሚበላለጡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ተከታታይ ድሉን ለማስመዝብ መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ ከሽንፈት ለማገገም ይፋለሙበታል።

ወልዋሎን በማሸነፍ ከድል ጋር የታረቁት ኢትዮጵያ መድኖች በውድድር ዓመቱ አንድ ድል፣ አንድ ሽንፈት እንዲሁም ሦስት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበዋል። ስድስት ነጥቦች መሰብሰብ የቻለው ቡድኑ በሦስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ በመውጣት ከስሑል ሽረና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጋራ በርከት ባሉ ጨዋታዎች የአቻ ውጤት ያስመዘገበ ቡድን ነው።

ካከናወናቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግቡን ያላስደፈረው መድን የተከላካይ ክፍሉ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። እስካሁን ድረስ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ ግብ ያላስተናገደው ቡድኑ ከሀብታሙ ታደሰ የግንባር ግብ ውጭ መረቡን ካለማስደፈሩም በተጨማሪ በጨዋታዎቹ የነበረው ተጋላጭነት አናሳ ነው።

በቅጣት እንዲሁም በጉዳት ምክንያት ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አምስት የተለያዩ የተከላካይ ጥምረቶች የተጠቀሙት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በእነዚህ ወቅቶች ዋነኛው የቡድኑ ጥንካሬ ይዘው መዝለቃቸው እንደ ትልቅ እመርታ የሚነሳላቸው ነጥብ ቢሆንም የማያኩራራ የማጥቃት ጥምረት የላቸውም። በአጭር ጊዜ የተወሃደው የአማካይ ክፍል አሁንም ዕድሎች እየፈጠረ ቢቀጥልም ኳስና መረብ ማገናኘት የቡድኑ ደካማ ጎን ነው። ቡድኑ በአምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የዚህ ማሳያ ነው።

ከቅርብ ሳምንታት እንቅስቃሴያቸው የወረደ ብቃት በማሳየት በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት ምዓም አናብስት ከውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈታቸው ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ከመጨረሻው መርሃግብር በፊት በተካሄዱ አራት ጨዋታዎች ውጤታማ የሚባል የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው መቐለዎች በብዙ ረገድ ተቀዛቅዞ የታየው የማጥቃት አጨዋወታቸው ማስተካከል እንዳለባቸው እሙን ቢሆንም ለተደጋጋሚ የግል ስህተቶች ተጋላጭ እየሆነ ያለውና በጉዳት እና በቅጣት የመነመነው የተከላካይ ክፍላቸው ድክመት መቅረፍ ቀዳሚ ስራቸው መሆን ይገባዋል። ቡድኑ በመጀመርያዎቹ አራት መርሃብሮች በጨዋታ በአማካይ ከአንድ ግብ በታች እያስተናገደ ከዘለቀ በኋላ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አራት ግቦች ማስተናገዱም የዚህ ማሳያ ነው።

በአምስቱም የሊጉ ጨዋታዎች ቢያንስ በአንድ የሜዳ ክፍል ላይ ለውጥ እያደረጉ ሲጫወቱ የታዩት መቐለዎች ጉዳት ከበረታባቸው የሊጉ ቡድኖች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በነገው ዕለትም ቡድኑ ካስቆጠራቸው ስድስት ግቦች አምስቱን ማስቆጠር የቻለው ያሬድ ብርሀኑ በጉዳት ምክንያት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ በመሆኑ እንዲሁም ተጋጣሚያቸው በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን ያስተናገደ ክለብ መሆኑ በፊት መስመር የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ ነው።

መቐለ 70 እንደርታዎች በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያሉት የመሀል ተከላካዮቹ መናፍ ዐወል እና ዮናስ ግርማይ አያሰልፉም ከዚህ በተጨማሪም ያሬድ ብርሀኑ እና ያሬድ ከበደ በጉዳት ምክንያት የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። ባለፈው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ያልተሰለፈው ሸሪፍ መሐመድ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑም ለቡድኑ መልካም ዜና ነው። በኢትዮጵያ መድን በኩል
የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት አለን ካይዋ እና ያሬድ ካሳዬ የነገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ይሆናል።

ሁለቱም ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።