በከፍተኛ ሊጉ ተሳታፊ የሆነው ሀምበርቾ ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ቁርጡ የለየለት መሆኑ ታውቋል።
በ2016 የውድድር ዘመን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳትፎ በማድረግ የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ሆኖ በማጠናቀቅ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ሀምበርቾ በሊጉ የነበረው ውስብስብ ችግር ባለመቀረፉ የክለቡ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ሆኗል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሀምበርቾ የክለብ ላይሰንሲግ መስፈርቱን እንዲያሟላ ተደጋጋሚ ቀነ ገደብ ቢሰጠውም ሳያሟላ በመቅረቱ በኢትዮጵያ ዋንጫ ከሸገር ሲቲ እንዲሁም በከፍተኛ ሊጉ ከእንጂባራ ከተማ እና ከወልቂጤ ከተማ ጋር ማድረግ የነበረበትን ጨዋታ ቡድኑ የሚጠበቅበትን አስገዳጅ መስፈርት ሟሟላት ባለመቻሉ ፎርፌ ሊሰጥበት ችሏል።
ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመርያ መሠረት አንድ ቡድን በአንድ የውድድር ዓመት ውስጥ በተለያየ የጨዋታ ጊዜ እና በተከታታይ ጨዋታ ሁለት ጊዜ ፎርፌ የሰጠ ከሆነ በተቀመጠው መመርያ ደንብ መሠረት ከውድድሩ ይሰረዛል ፣ ከሊጉ ወደ ታችኛው ዕርከን ወርዶ እንዲጫወት ይደነግጋል። በዚህ መነሻነት በቀጣይ የእግርኳሱ የበላይ አካል የሚወሰነው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ ሀምበርቾ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት የሚጣልበት እና ከከፍተኛ ሊጉ ውድድር የሚሰረዝ ሲሆን ወደ አንደኛ ሊግ ወርዶ እንዲጫወት ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሀምበርቾ በኩል የክለቡን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ ምን እየታሰበ ነው በሚል የክለቡ አመራሮች ካሉ በማለት ጥያቄ ለማቅረብ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።