ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድኖች ምዓም አናብስትን ረምርመዋል

በምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን መቐለ 70 እንደርታን 4ለ0 በሆነ ሰፊ ግብ ልዩነት በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አሳክቷል።

ኢትዮጵያ መድኖች ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ከረቱበት ቋሚ አሰላለፋቸው በረከት ካሌብን እና መሃመድ አበራን አሳርፈው ዋንጫ ቱትን እና አቡበከር ሳኒን ይዘው ሲገቡ መቐለ 70 እንደርታዎች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሽንፈት ካስተናገዱበት ቋሚያቸው አምስት ለውጦችን በማድረግ ሰለሞን ሀብቱ፣ ሄኖክ አንጃው፣ ያሬድ ከበደ፣ ያሬድ ብርሃኑ እና ቦና ዓሊን አስወጥተው በአንተነህ ገብረክርስቶስ ፣ሸሪፍ መሐመድ፣ ኪሩቤል ኃይሉ፣ ክብሮም አፅብሃ እና ብሩክ ሙሉጌታ ተክተው ቀርበዋል።

ቀዝቃዛ የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየበት በመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃ ሁለቱም ቡድኖች የተሳካ የኳስ ቅብብል ሲያደርጉ አልተስተዋሉም። ኢትዮጵያ መድን አልፈው አልፈው ወደፊት ለመሄድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ምዓም አናብስቶች በጥንቃቄ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመጫወት ኳስን ሲያርቁ ታይተዋል። በረጃጅም ኳሶች ወደ ምዓም አናብስት ግብ አካባቢ የደረሱት መድኖች የመጀመሪያ ግባቸውን በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረዋል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ ንጋቱ ገብረሥላሴ ከተከላካይ ጀርባ ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በመድረስ ከመቐለ 70 እንደርታ ግብ ጠባቂ ሶፎንያስ ሰይፈ ጋር በመገናኘት ሙከራ ለማድረግ ሲጥር ከግብ ጠባቂው ጋር በተፈጠረ ንክኪ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ዳዊት ተፈራ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መድኖችን መሪ መሆን ችሏል።

ጨዋታው ግብ ከተቆጠረ በኋላ ትንሽ መነቃቃት ታይቶበታል። ኢትዮጵያ መድን ኳስ መስርተው ከግብ ጠባቂያቸው ጀምሮ ሲያንሸራሽሩ ተስተውለዋል። መቐለ 70 እንደርታዎች በአንፃሩ በአጫጭር ኳስ ቶሎ ቶሎ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ቢደርሱም መድኖች ባሳዩት ጥሩ መከላከል ሁነኛ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። በ28ኛው ደቂቃ ዒላማውን የጠበቀ የሚባለውን ሙከራ ብሩክ ሙሉጌታ ከሳጥን ውጭ ሆኖ ሲያደርግ አቡበከር ኑራ በቀላሉ ተቆጣጥሮታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት አቡበከር ሳኒ በመስመር በኩል ያሻገረውን ኳስ አብዲሳ ጀማል ያመከነው አጋጣሚ ምናልባትም የመድኖችን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ ነበር።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ኢትዮጵያ መድን ጠንከር ብለው ተመልሰው በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ግብ በማስቆጠር ብልጫ ወስደዋል። ምዓም አናብስቶች ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ አድርገው ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል። መድኖች ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ሁለተኛ የሆነችዋን ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሁለት ደቂቃ ብቻ የፈጀባቸው ሲሆን በ47ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። አቡበከር ሳኒ በቀኝ መስመር በኩል ኳስ እየገፋ ሄዶ ወደ ግብ አሻግሮ አብዲሳ ጀማል ጨርፎ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው ተፍቷት ተሻግሮ ብቻውን ነፃ ሆኖ ሲጠባብቅ የነበረው ረመዳን የሱፍ በቀላሉ መረብ ላይ አክሏታል።

ግቦችን ለማስቆጠር አዘውትረው ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ የደረሱት መድኖች ሌላኛዋን ግብ በ65ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። ሀይደር ሸረፋ ከግብ ክልላቸው አካባቢ በረጅሙ ለረመዳን የሱፍ ሰንጥቆለት ረመዳን የሱፍ በግሩም ሁኔታ ወደ ሳጥን አሻግሮ አብዲሳ በጥሩ አጨረረስ ሦስተኛዋን ግብ ከመረብ ጋር አገናኝቷል። በዚህ ብቻ ያላበቁት መድኖች አራተኛዋን ግብ ለማስቆጠር አራት ደቂቃ ብቻ ጠብቀው በ70ኛው ደቂቃ ላይ በዳዊት ተፈራ አማካኝነት አግኝተዋል። በግራ ማዕዘን በኩል ጋቶች ፓኖም እና ረመዳን የሱፍ የአንድ ለአንድ ቅብብል አድርገው ረመዳን የሱፍ ከፍ አድርጎ ወደ ግብ አሻምቶ ዳዊት ተፈራ በግንባሩ ገጭቶ የጨዋታውን አራተኛ ግብ ለእራሱ ሁለተኛዋን ግብ አስቆጥሯል።

በአጋማሹ ኢትዮጵያ መድኖች ፍፁም የጨዋታ የበላይነት ወስደው እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ጫና ሲያሳድሩ ታይተዋል። መቐለ 70 እንደርታዎችም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ካስተናገዱት ግብ አንፃር ተስፋ በመቁረጥ ስሜት እንቅሰቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። እንዲሁም ወደ ግብ ለመድረስ ያደረጉት ጥረት መድኖች ባደረጉት የመከላከል አደረጃጀት ሊሳካላቸው አልቻለም። ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 4ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።