ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፋሲል ከነማን ረቷል

ጥሩ ፉክክር እና አምስት ግቦችን በተመለከትንበት ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ለ2 በሆነ ውጤት ፋሲል ከነማን በመርታት ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

ፋሲሎች ከአርባምንጩ ሽንፈታቸው በአራቱ ተጫዋቾች ላይ ለውጥ ሲያደርጉ አትርሳው ተዘራ ፣ እዮብ ማቲዮስ ፣ አፍቅሮት ሠለሞን እና ማርቲን ኪዛ አርፈው ዮናታን ፍሰሀ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ጃቢር ሙሉ እና ዳግም አወቀ ተተክተዋል ሀዋሳን ያሸነፉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው አሸናፊ ጥሩነህን በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ብቸኛ ቅያሪያቸው በማድረግ ገብተዋል።

ፈጠን ባሉ ማጥቃቶች የመጀመሪያውን ሀያ ደቂቃዎች ለመጫወት ጥረት ያደረጉት አፄዎቹ 10ኛው ደቂቃ ላይ ነበሮ ጎል ያስቆጠሩት። ከግራ ጃቢር ሙሉ ካደረገው አንድ ሁለት ንክኪ በኋላ ጥሩ አድርጎ መሬት ለመሬት ያቀበለውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ እድሪሱ መረብ ላይ አሳርፏታል። አማካይ ክፍሉ ላይ ብልጫውን በመውሰድ ለአጥቂዎች በተከላካዮች መሐል ለመሐል በሚሰነጠቁ ኳሶች ለመጫወት የሞከሩት ፋሲሎች 17ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ በዚሁ የጨዋታ መንገድ የሰጠውን አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂው እድሪሱ አብዱላሂ ጋር የተገናኘው ቃልኪዳን ዘላለም ወርቃማዋን አጋጣሚ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።

ቀስ በቀስ የመስመር አጠቃቀማቸውን እያሳደጉ የመጡት እና በጥልቀት ወደ ሳጥን ተስበው መንቀሳቀስን የጀመሩት ኤሌክትሪኮች በፍቃዱ አለሙ ፣ ሽመክት ገግሳ እና አቤል ሀብታሙ አማካኝነት አከታትለው ካደረጓቸው ሙከራዎች በኋላ ጨዋታው ሊገባደድ በጭማሪው 45+2 ላይ ሽመክት ከቀኝ እየነዳ ያቀበለውን ፍቃዱ በተከላካይ መሐል አሳልፎ የሰጠውን አቤል ሀብታሙ የአቻነት ጎል በማድረግ አጋማሹ 1ለ1 ተገባዷል።

ተመጣጣኝ ፉክክርን ማስመልከት የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ፋሲሎች በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ የእንቅስቃሴ የበላይነት ቢኖራቸውም ጎል ያስቆጠሩት ግን ኤሌክትሪኮች ናቸው። አፄዎቹ ጌታነህ ከበደ ከመስመር የተሻማለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በግብ ጠባቂው እድሪሱ ተጨርፋ ወደ ማዕዘንነት ተቀይራ ኳስ ተመታ በተከላካይ ተገጫጭጭ ስትመለስ ያገኘው ሽመክት ጉግሳ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ የግብ ጠባቂው ኦማስ ኦባሶጊ ከግብ ክልሉ ለቆ መውጣት ያገዘው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የልጅነት ቡድኑ ላይ በድንቅ አጨራረስ ጎልን በማከል ኢትዮ ኤሌክትሪክን ወደ መሪነት አሸጋግሯል።

ማራኪ እንቅስቃሴዎችን እያስመለከተን የተጓዘው ቀጣዮቹም ደቂቃዎች በይበልጥ በሁለቱም በኩል በመስመሮች በኩል በቶሎ ወደ ሳጥን በሚደረጉ አጨዋወቶች አደገኛ የሚባሉ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት የተደረጉበት ነበር። 75ኛው ደቂቃ ከግራ የሳጥን ጫፍ ናትናኤል ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠን የቅጣት ምት ያሬድ የማነ ወደ ጎልነት ለውጦ የኤሌክትሪክን መሪነት ወደ ሦስት አሳድጓል።

በጥሩ ግለት በፉክክር እየታጀበ 77ኛው ደቂቃ ሲደርስ አፄዎቹ አንዋር ሙራድ ወደ ቀኝ የሰጠውን ኳስ ጌታነህ ከበደ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ካደረገ በኋላ ጨዋታው በመጨረሻም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ለ2 አሸናፊነት ተቋጭቷል።