ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና ስሑል ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል

ጠንካራ ፉክክር ያስመለከተው የኢትዮጵያ ቡናና የስሑል ሽረ ጨዋታ ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ቡና በስድስተኛው ሳምንት መቐለ 70 እንደርታን ከረቱበት ቋም አሰላለፋቸው አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ስንታየሁ ዋለጬን በሚኪያስ ፀጋዬ ቀይረው ሲገቡ ስሑል ሽረ በአምስተኛው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ሽንፈት አስተናግደው ወደ እረፍት ካመሩበት ቋሚያቸው ሁለት ለውጥ በማድረግ ጥዑምልሳን ሀ/ሚካኤልን እና አልአዛር አድማሱን አሳርፈው መሐመድ ሱሌይማን እና አሌክስ ኪታታን ቋሚያቸው ውስጥ አስገብተው ቀርበዋል።

ተመሳሳይ ይዘት ባለው በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖቸ ኳስ በማንሸራሸ የተሻለ የኳስ ብልጫ ለመውሰድ የጣሩበት ሲሆን ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ወደፊት በመሄድ ተመጣጣኝ አካሄድ ያሳዩበትም ነበር። በ19ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች ያደረጉት አደገኛ ሙከራ ሲታወስ አማኑኤል አድማሱ ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ መጥቶ ለትንሽ ከፍ ብሎበታል። ስሑል ሽረ በበኩሉ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ቢሆን መሪ የሆኑበት ግብ ለማስቆጠር ሀያ አምስት ደቂቃ ጠብቀዋል። በ26ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል። በቀኝ መስመር በኩል ነፃነት ገብረመድህን የኢትዮጵያ ቡናን ተጫዋቾች በቀላሉ አታሎ በማለፍ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ ፋሲል አስማማው ዘሎ በእግር በመንካት ከመረብ ጋር አገናኝቶ ስሑል ሽረን መሪ አድርጓል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደፊት ገፍተው ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የግብ እድል ለመፍጠር ጥረዋል። ስሑል ሽረም በአንፃሩ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት በመልሶ ማጥቃት እላማውን የጠበቀ ባይሆንም የግብ ማግባት ሙከራዎች ሲያደርግ ለመመለከት ተችሏል። በአጋማሹ ስሑል ሽረዎች እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል የሚገቡ ቢመስልም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የእራሳቸው ተጫዋቾች የሰሩት ጥፋት ግብ ለመቆጠሩ ምክንያት ሆነዋል። አጋማሹ ሊጠናቃቅ ተጨማሪ በታየው ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ሙከራ በሚያደርጉበት ወቅት የስሑል ሽረ ተከላካዮች ባደረጉት በእጅ ንክኪ ፍፁም ቅጣት ምት አግንተው አንተነህ ተፈራ መረብ ላይ አሳርፎ አጋማሹን ነጥብ በመጋራት ወደ መልበሻ ክፍል እንድገቡ ሆኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጠንከር ብለው ሲመለሱ ኢትዮጵያ ቡና በአንፃራዊነት የግብ ማግባት እድል በመፍጠር ረገድ ተሽለው በመገኘች በተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ሳያሳካላቸው ደቂቃዎች ገፍተዋል። በ63ኛው ደቂቃ ላይ አንተነሀ ተፈራ  ከመስመር የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ የግብ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ሲታወስ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ወደ አንድ ጎን እንዲያደላ ለማድረግ የተቃረበ አጋጣሚም ነበር። ስሁል ሽረዎችም በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት በፈጣኝ ሽግግር ወደ ቡናማዎቹ ግብ ክልል ስደርሱ ተስተውለዋል።

በአጠቃላይ አጋማሹ ምንም እንኳን ቡድኖቹ ጠንከር ብለው በመግባት ግብ ለማስቆጠር የጣሩበት ቢሆንም ከሱም በተጨማሪ ጎን ለጎን ግብ ላለማስተናገድም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ጠንካራ የመከላከለ ፉክክር ያስመለከቱበት ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስመለከት 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተቋጭቷል።