ሊጉ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ምክንያት ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት የሚደረጉትን የ7ኛ ሳምንት መገባደጃ መርሃግብሮችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፍ ቀርበዋል።
ድሬዳዋ ከ ሀድያ ሆሳዕና
ለሳምንታት ድል የተራቡ ቡድኖች የሚያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ተከታታይ ሁለት ድሎች ካስመዘገቡ በኋላ ላለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት ብርቱካናማዎቹ ከድል ጋር ለመታረቅ በተመሳሳይ አራት ድል አልባ ሳምንታት ካሳለፉት ነብሮቹ ጋር ይፋለማሉ።
በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ያሳኩት ድሬዎች እንቅስቃሴያቸው በውጤት ማጀብ አልቻሉም። ቡድኑ በአፈፃፀም ላይ ቀላይ የማይባሉ ክፍተቶች ቢኖሩትም አሁንም በማጥቃቱ ረገድ ያለው አወንታዊ ጎን ይዞ መቀጠሉ እንደ ጠንካራ ጎን የሚወሰድ ቢሆንም በመከላከሉ ረገድ የተስተዋሉት ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ ግድፈቶችን አርመው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ከዚ ቀደም ተደጋጋሚ የቅብብል ስህተቶች እንዲሁም የተጋጣሚን አጨዋወት ከግምት ውስጥ ያላስገባ የተከላካዮች መስመር ‘High line’ እና መሰል የመከላከል ክፍተቶች የታየበት ቡድኑ በነገው ጨዋታ ድክመቶቹን አርሞ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በሊጉ መክፈቻ ዕለት መቐለን ካሸነፉ ወዲህ ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከተከታታይ የሽንፈት እና የአቻ ውጤቶች ለመላቀቅ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ሊጉን በጀመረበት የድል መንገድ ማስቀጠል ያልቻለው ቡድኑ በጨዋታ በአማካይ አንድ ግብ ያስተናገደው እና ከዚ ቀደም በጠንካራነቱ ተጠቃሽ የነበረው የመከላከል አደረጃጀቱ ጥንካሬ ማስቀጠል አልቻለም። ከዚ በተጨማሪም
በአምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስቆጠር የቻለው የፊት መስመሩ እንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ሆኖ ሳለ ጥምረቱ ሁነኛ ግብ አስቆጣሪ ማጣቱ
የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ማስረጃ መሆን ይችላሉ። በፊት መስመሩ ያሉት በጎ ነገሮች ለነገ ጨዋታ ይዞ መሄድ የሚገባው መልካም ጎን ቢሆንም በተከታታይ ጨዋታዎች ወደ አሸናፊነት መምጣት መቸገሩ ግን አሁንም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
ድሬዳዋ ከተማዎች ከቅጣትም ሆነ ጉዳት ነፃ የሆነው ስብስባቸው ይዘው ለነገው ጨዋታ ሲቀርቡ ሀድያ ሆሳዕናዎች ግን በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው ጫላ ተሺታን ጨምሮ ተመስገን ብርሀኑ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ፣ ሄኖክ አርፊጮ እና በረከት ወንድሙ በነገ ጨዋታ አያሰልፉም።
ቡድኖቹ በሊጉ 10 ጊዜ ሲገናኙ 4 ጊዜ ተሸናንፈው
2 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። 28 ግቦች በተስተናገዱበት ግንኙነት ሀድያ ሆሳዕና 15 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 13 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ወልዋሎ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የውድድር ዓመቱ አይን ገላጭ ድል ፍለጋ ላይ ያለው ወልዋሎ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ከድል ጋር ከተራራቁት ሻምፕዮኖቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ የሳምንቱ መገባደጃ መርሀ-ግብር ነው።
በምንም ነጥብ በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ወልዋሎ ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ጋር ከተለያየ በኋላ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደርጋል።
ከነጥብም ባሻገር በብዙ መመዘኛዎች ከሌሎች የሊጉ ክለቦች ጋር ሲነፃፀር በቂ በሚባል የውህደት ደረጃ የማይገኙት ቢጫዎቹ በአሁናዊ የሰንጠረዡ አቀማመጥ መሰረት በሊጉ ለመቆየት ከሚያስችላቸው ከ14ኛ ደረጃ በ7 ነጥብ ርቀው ይገኛሉ፤ በመሆኑም ከወዲሁ የተፈጠረው ርቀት
ለማጥበብ በነገው ጨዋታ ለማሸነፍ ቅድሚያ ሰጥተው መቅረብ ግድ ይላቸዋል። ላለፉት ሁለት ቀናት ቡድኑን በጊዝያዊነት ተረክበው ልምምድ በማሰራት ላይ የሚገኙት ሁለቱም አሰልጣኞች ከወዲሁ በነገው ዕለት ይዘውት የሚገቡትን አጨዋወት ለመገመት አዳጋች ቢሆንም ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር ለመከላከል ቅድምያ የሰጠ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል።
ከዚ በተጨማሪ ግብ ጠባቂው በረከት አማረን በቅጣት ያጡት ወልዋሎዎች ባለፈው ዓመት በትግራይ ዋንጫ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ባሳየው ሚካኤል ታደሰ ተክተው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በመጀመርያው መርሀ-ግብር አርባ ምንጭን ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ንግድ ባንኮች ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ሻምፕዮኖቹ በዋነኝነት ኳስ መቆጣጠር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ለመተግበር እየጣሩ ቢገኙም የፈት መስመራቸው አሁንም የሚፈለገው ስኬት ላይ አልደረሰም። ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች በማስቆጠር መልካም አጀማመር ማድረግ ቢችልም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠረው የግብ መጠን አንድ ብቻ ነው። በነገው ዕለት በአምስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ያስተናገደ እና ከባለፉት ተጋጣሚዎች አንፃር ደካማ የመከላከል ቁጥሮች ያስመዘገበ ቡድን እንደመግጠማቸው የሚጠብቃቸው ፈተና ከባድ ይሆናል ተብሎ ባይጠበቅም የነገው ውጤት በቅርብ ሳምንታት ከጨዋታ ብልጫ በዘለለ ግቦችን ማስቆጠር ለተሳነው ቡድን ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።
አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ባለፉት ሁለት ጨዋታም ለተጋጣሚ መከላከል አመቺ የነበረ ተገማች የማጥቃት አጨዋወቱንም ቀርፎ መምጣት ይጠበቅበታል።
በወልዋሎ በኩል ጉጨም ላይ የቆዩት ስምዖን ማሩ እና ስምዖን ተኽለ ጨምሮ ሳምሶን ጥላሁን እና ናትናኤል ኪዳነ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይሰለፉም፤ አምበሉ በረከት አማረም በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩልም ኤፍሬም ታምራት በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።