ሀምበርቾ ውሳኔ ተላልፎበታል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር አዘጋጅ እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በሀምበርቾ ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ አሳልፏል።

በ2016 በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ከሆነ በኋላ በመጣበት ዓመት ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች እየታመሰ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ወደ ከፍተኛ ለመውረድ የተገደደው ሀምበርቾ በኢትዮጵያ ዋንጫ አንድ እንዲሁም በከፍተኛ ሊጉ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ሳይቀርብ ቀርቶ በፎርፌ ተሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ ከትናንት በስቲያ ባስነበብናችሁ ጥንቅር መሠረት ቡድኑ ውሳኔ ተላልፎበታል።

በዚህም መሠረት ሀምበርቾ እግር ኳስ ቡድን ጥቅምት 17 2017 ከእንጅባራ እግር ኳስ ቡድን እና ጥቅምት 23 2017 ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ቡድን ጋር በነበረዉ ጨዋታ የሀምበርቾ እግር ኳስ ቡድን 2 ጊዜ በተከታታይ ወይም በዚያው የውድድር ዓመት በተለያየ ጊዜ በጨዋታ ሜዳ ባለመገኘቱ ፎርፌ በመስጠታቸው በተሻሻለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ ምዕራፍ 3 አንቀጽ 69 ተራ ቁጥር 14 መሰረት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር መሰረዛቸዉን ኮሚቴው ወስኗል፡፡

በተጨማሪም የጨዋታ ፕሮግራም ወጥቶለት በሰዓቱ ቀርቦ ውድድሩን ያላከናወነው ሀምበርቾ እግር ኳስ ቡድን በ2017 ለውድድሩ ማስፈጸሚያ በወጣው ደንብ አንቀጽ 5 ተራ ቁጥር 3 እና 5 መሰረት ብር 60,000 (ስልሳ ሺህ ብር ቅጣት 26/02/17 እስከ 03/03/17 ድረስ ባሉት 7 ቀናት ዉስጥ በቅጣት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገቢ እንዲያደርግ ተወስኗል።

በተያያዘ ዜና የእንጅባራ ከተማ እና የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ቡድኖች ከሀምበርቾ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ሀምበርቾ ሜዳ ላይ ባለመገኘቱ የፎርፌ አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል። ሆኖም ሀምበርቾ ከውድድር መሰረዙን ተከትሎ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት በእለቱ ያገኙት ውጤት እንደማይመዘገብ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር አዘጋጅ እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡