ሪፖርት | የአዲስ ግደይ ጎሎች ለንግድ ባንክ ወሳኝ ነጥብን አስገኝተዋል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከመመራት ተነስተው በአዲስ ግደይ የሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ግቦች ወልዋሎ ዓ.ዩ 2ለ1 በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በመሩት የመጨረሻ ጨዋታ በመድን ሽንፈት የገጠማቸው ወልዋሎዎች ለዛሬው ጨዋታ በረከት አማረን በናትናኤል ኪዳኔ ፣ ጋዲሳ መብራቴን በሱልጣን በርሄ ሲቀይሩ በተመሳሳይ በመጨረሻ ጨዋታቸው በመቻል የተረቱት ንግድ ባንኮች ደግሞ ሱለይማን ሀሚድ እና ብሩክ እንዳለን አሳርፈው ቢኒያም ካሳሁን እና ሳይመን ፒተር በቋሚ አሰላለፍ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የመጀመሪያዎቹን አምስት ደቂቃዎች ብልጫን መያዝ የቻሉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 2ኛው ደቂቃ ኪቲካ ከቀኝ ወደ ውስጥ የሰጠውን ኳስ ሳይመን ፒተር ከግብ ጠባቂ ጋር በአንድ ለአንድ ተገናኝቶ የግብ ዘቡ ናትናኤል ኪዳኔ ፈጣኗን ሙከራ መክቷታል። ንግድ ባንኮች በሁለቱም መስመሮች በኩል የኪቲካ እና ሳይመንን እንቅስቃሴዎች ተጠቀመው ወደ ሳጥን በይበልጥ በመጠጋት ለመንቀሳቀስ ወልዋሎዎች በበኩላቸው አጥቂዎቻቸውን ያማከሉ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት ምርጫቸው በማድረግ መንቀሳቀስ ቢችሉም ጨዋታው ከነበረው ወረድ ያለ ፉክክር አንፃር በግብ ሙከራዎች ረገድ ያልታደለ ነበር።

21ኛው ደቂቃ ላይ በወልዋሎ በኩል በረጅም ኳስ ያገኛትን አጋጣሚ ከግራ መስመር አክርሮ ዳዋ የመታትን ኳስ ፍሬው ያወጣበት እና በንግድ ባንክ በኩል አዲስ ግደይ በቀጥታ የመታትን ኳስ ናትናኤል ያወጣበት አጋጣሚዎች በሙከራ ረገድ ሊጠቀስ የሚችሉ ቢሆንም በአጋማሹ ምንአልባትም 44ኛው ደቂቃ አማካዩ ባሲሩ ዑመር በጉዳት በብሩክ እንዳለ የተተካበት በልዩነት የምትነሳዋ ክስተት ነበረች።

ከዕረፍት መልስ ቀዝቀዝ ብሎ በተመለሰው ጨዋታ በይበልጥ በሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴም የተዳከመ ነበር።

ወልዋሎዎች በ58ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ያቀበለውን ኳስ ዳዊት ገብሩ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎ ቢጫዎቹን ቀዳሚ አድርጓል ፣ ከጎሏም በኋላ ቡልቻ ሹራ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በፍሬው ጌታሁን ተመልሶበታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሲያደርጉት እንደነበረው የመስመር አጨዋወት ወደ መጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች የተመለሱት ንግድ ባንኮች 71ኛው ደቂቃ ላይ ታዬ ጋሻው ሳይመን ፒተር ላይ በሳጥን ውስጥ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አዲስ ግደይ በማስቆጠር ሀምራዊ ለባሾቹን ወደ 1ለ1 ሲያሸጋግር ሁለት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ ከሳይመን ፒተር ያገኛትን ኳስ አዲስ ግደይ ድጋሚ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል በማድረግ በቀሩት ደቂቃዎችም ጨዋታው የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊነት ተቋጭቷል።