👉 “ከምድባችን የማለፍ ዕቅድ ነው ያለን።”
👉 “የካፍ ፕሮግራም በጊዜ አለመታወቅ በዕቅድ እንዳንጓዝ አድርጎናል።”
👉 “ታሪክ ለመሥራት ጉጉት እንዳለ ተጫዋቾቼ ጋር ፣ እኔም ጋር ሆነ ሁሉም ጋር ይታያል።”
👉 “እዚህ ውድድር ላይ አቅማቸውን እናያለን ብለው ከተጫዋቾቹ ጋር በቀጥታ የተነጋገሩ እኛንም ያሳወቁ አሉ።”
👉 “ተጫዋቾቼ ወርቅ ናቸው። በተጫዋቾቼ ነው እዚህ የደረስኩት።”
👉 “ካመጣነው ውጤት አንጻር ሴቶቹን የማበረታታት እና ሞራል የማነሳሳት ነገር አልታየም።”
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒየን ሆነው በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ ዞን የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ማጣርያም ቻምፒየን በመሆን ለካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ አልፈው በመጪው እሁድ ውድድራቸውን የሚጀምሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ትናንት ሌሊት ወደ ሞሮኮ ማቅናታቸው የሚታወስ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።
የዝግጅታችሁ ሂደት?
“ዝግጅት 23 ቀን ነው የሠራነው ፤ 2 ቀን አዲስ አበባ 21 ቀን ደግሞ አዳማ ላይ ሠርተናል። ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከወንዶች ጋር አድርገናል። ከወንዶች ጋር መጫወት በቂ ልምድ ስላልሆነ ብዙ ክፍተቶቻችንን ያሳየናል ማለት አይደለም። በተወሰነ መልክ ግን ካለማድረግ ይሻላል።”
የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ጥረት አላደረጋችሁም ነበር?
“ጥረት አድርገን ነበር። ግን የሊጉ ውድድር ፕሮግራም ሲወጣ አልመቻች አለ እንጂ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት የምንገጥመው ከነበረው መቻል ጋርም የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ጥረት አድርገን ነበር። የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከተመሠረተ ጀምሮ እንደዚህ በቶሎ ሲጀምር ዐይቼ አላውቅም። ሁለት ሦስት የወዳጅነት ጨዋታ እናደርጋለን ብለን አቀድን ነበር ግን ካፍም ዘግይቶ ነበር ያሳወቀን። በዚህ የተነሳ በሴካፋ ዞን ጠንካራ ከነበሩት እነ ሲምባን ጨምሮ የወዳጅነት ጨዋታ ከእነሱ ጋር ለማድረግ ነበር ሀሳባችን ግን የካፍ ፕሮግራም በጊዜ አለመታወቅ በዕቅድ እንዳንጓዝ አድርጎናል።”
ከሴካፋ ዞን ውድድር ተነስታችሁ አሁን ላይ ያደረጋችሁት ዝግጅት ምን ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር?
“አንድ ወር ዕረፍት አድርገናል። ፕሮግራሙን ስለማናውቅ ቀድመን መጀመር አልቻልንም ፤ ቀድመን ያውቅነውም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ነበር። በ23 ቀን ብዙ ተአምር እንለውጣለን ባንልም ግን ተጫዋቾቻችን በሴካፋ ዞን ቻምፒየን ስለሆኑ አስተሳሰብ ላይ ለውጥ ለማምጣት ታግለናል። ፊዚካል ፊትነስ ፣ ቴክኒካል እና ታክቲካል ነገሮችን ይበልጥ ለማሻሻል በ23 ቀናት ጥረናል። የአፍሪካ እግርኳስ በአብዛኛው ተመሳሳይ ነገር አለው ግን ወደ ምዕራቦቹ ስትሄድ ትንሽ ፍጥነት እና ጥበብ ይጨምራል። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ወደ አውሮፓ ሄደው ሲጫወቱ ቆይተው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ናቸው። ብዙ ልምድ ካካበቱ ቡድኖች ጋር ነው የምንጫወተው።”
በቡድኑ አባላት ዘንድ ለውድድሩ ያለው ዝግጁነት እንዴት ይገለጻል?
“ተጫዋቾቼ ላይ ጥሩ ስሜት አለ ለውድድሩ ፤ የተወሰኑ ጉዳቶች ነበሩ ከዚህ በፊት ፤ ሴናፍ ጉዳት ላይ ነበረች ግን አገግማ ሙሉ ትሬኒንግ ሠርታለች ፣ ቅድስት ጉዳት ላይ ነው ያለችው በመጨረሻ ቀን ነው ወደ ሜዳ የተመለሰችው። የተጎዱ የሚታወቁ ሦስቱ ተጫዋቾች አሉ መዲና ዐዎል ፣ ብዙዓየሁ ታደሰ እና የዓምና የሊጉ ኮከብ ሲሣይ ገብረዋህድ ጉዳት ላይ ናቸው ይህም በተወሰነ መልኩ አስቸግሮን ነበር ግን እዛ ሄደን ታሪክ ለመሥራት ጉጉት እንዳለ ተጫዋቾቼ ጋር ፣ እኔም ጋር ሆነ ሁሉም ጋር ይታያል።”
ውድድሩ የሚፈጥርላችሁ ዕድል…
“እንደሚታወቀው ለእኔም ለተጫዋቾቼም የመጀመሪያ ነው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ፤ በውድድሩ ላይ በርካታ መልማዮች ይኖራሉ። ሱፐር ስፖርትም በቀጥታ ስርጭት እንደሚያስተላልፍ ይታወቃል። ይህ ደሞ ለተጫዋቾች ጥሩ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዐብዮቱን መጀመሩ ይታወቃል። ተጫዋቾችን ወደ አሜሪካ እና ታንዛኒያ ልኳል አሁንም ደግሞ ከአውሮፓ የመጡ ጥያቄዎች አሉ እና እዚህ ውድድር ላይ አቅማቸውን እናያለን ብለው ከተጫዋቾቹ ጋር በቀጥታ የተነጋገሩ እኛንም ያሳወቁ አሉ።”
ስለ ምድብ ድልድሉ…
“በመጀመሪያ የማሜሎዲ ሰንዳውንስ ሙሉ መረጃ አለን በተጨማሪም ሌላ ቡድን ጋር ስለምንጫወት እነሱን ቀድመን የማየቱ ዕድል አለን። ይሄ የሞት ምድብ ነው። በአፍሪካ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ውድድሮች ጠንካራ እና ያለንበት ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ብዙ ዕውቀት ፣ ብዙ ልምድ እና ብዙ ችሎታ እንቀበላለን ምክንያቱም አቅማችንን ዐይተን ብዙ ነገር ለመሥራት የምንረዳበት ይሆናል። የቱ ጋር እንዳለን የሚጠቁመን ጥሩ አጋጣሚ ነው። የተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ አንተን የሚያስተምር ነውና ከራሳችንም እንማራለን።”
ከሴካፋ ዞን ውድድር ይሄ በምን ይለያል?
“ሁሉም የተሟሉ ናቸው። ያው እኛጋ ገና እየተሟላ ነው ፤ እሱንም ቢሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው ያደረገው። ብዙዎቹ ፕሮፌሽናል ሜንታሊቲ ያላቸው ናቸው። መረጃ በደንብ ባይኖረኝም አሁን ከምንሄደው እኛ ብቻ ይመስለኛል ምንም ዓይነት ፕሮፌሽናል ተጫዋች የሌለን እና ይሄም የተለየ ነገር ይፈጥራል ብዬ ነው የማስበው።”
በውድድሩ ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?
“የመጀመሪያ ዕቅዳችን የነበረው ውድድሩ ላይ መሳተፍ ነው እሱን አሰክተናል። አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እና ምሥራቅ አፍሪካን የሚያሳይ አቅም ያለው ቡድን በየ ዲፓርትመንቱ ማሳየት እና ከምድባችን የማለፍ ዕቅድ ነው ያለን።”
ሴካፋ ውድድር ላይ ከፌዴሬሽኑ ጀምሮ የነበረው የሞራልም ሆነ የዕውቀት ድጋፍ አሁን ላይ ቀጥሏል ወይስ?
“እኔ መናገር የምችለው እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተገቢውን ታይቶ የማይታወቅ ማበረታቻ ሰጥቶናል ፤ እንኳን በሴቶች በወንዶች ታይቶ የማይታወቅ ነው ፤ የተግባር ቡድን እንደሆነ ዐሳይቶናል። በሌላ በኩል ምንም ዓይነት ነገር አልደረሰኝም ፤ ይሄ ንግድ ባንክ ስለሆነ አልጠብቅም። እንደ ሀገር ግን ካመጣነው ውጤት አንጻር ሴቶቹን የማበረታታት እና ሞራል የማነሳሳት ነገር አልታየም። ለምን እንደዚህ እንደቀዘቀዘ አላውቅም። ያው ግን ንግድ ባንክ ስላስደሰተን ያን ያህል ምንም ማለት አይደለም። እግርኳሱ ከተመሠረተ ጀምሮ በዚህ ደረጃ ብዙ ደጋፊዎች ያሏቸው ትልልቅ የሀገራችን ክለቦች እንኳ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተው ከቦሌ በቀይ ምንጣፍ ሲቀበሏቸው ያየሁ እኛን ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው በቀይ ምንጣፍ የተቀበለን እና በተለይ በሴቶች በኩል ሴቶቹን የሚያበረታቱ ተጨማሪ ድጋፎች ቢደረጉ ብዬ ነው የማስበው። ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከልብ ነው የማመሰግነው።”
“ከሰሞኑ የ25ኛ ዓመት የአሰልጣኝነት ሕይወትህን የሚዘግብ “የኮራ ሰው” የሚል ፊልም ተመርቋል ፤ ከስያሜው ጀምሮ ፕሮግራሙ እንዴት ነበር?
“ኮራ ማለት ወንዝ ናት ፤ ብሔር እና ሃይማኖት የሌላት ፤ ብዙ ሽማግሌዎች ሰው የሚያስታርቁባት እና ልጆች ደግሞ አፍ የሚፈቱባት ቦታ ናት። እናም ያደግኩበትን ቦታ ለማስታወሻ ይቀመጥልኝ ብዬ ነው ያን ርዕስ የሰጠሁት። በጣም ደስ ካለኝ ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠኝ ምላሽ ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ሚዲያን እጅግ በጣም ነው የማመሰግነው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሙሉ ስፖንሰር አድርጎኛል። ፊንጫ ኪዳነምሕረትንም Three brothersንም ሌሎችም በጓደኞቼም ወንድሞቼም በጣም ነው ሞቅ ያለው እና 25 ዓመት ሙሉ በእግርኳስም በሕይወቴ ውስጥ የነበረውንም በሙሉ ጠቅለል አድርጌ በ30 ደቂቃ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። መቼም ሕይወት ያልፋልና ታሪክ እና ሰነድ ማስቀመጥ የሚመጣው ትውልድ እኔም ለካ እንደዚህ መሥራት እችላለሁ ብሎ በደንብ እንዲሄድ ያስችላል እና እኔም በጣም ደስተኛ ነኝ ይሄንን በመሆኔ። ከ10 ዓመት በፊት መጽሐፍ ጽፌያለሁ አሁን ደግሞ ይሄንን ዘጋቢ ፊልም አስመርቂያለሁ በጣም ደስ ብሎኛል።”
ያልጠበከው ስጦታ ወይም ለየት ያለ አጋጣሚ?
“የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾቼን አልጠራኋቸውም ነበር። እንዳይመጡም ብዬ መልዕክት አስተላልፌ ነበር በኮቺንግ ስታፍ አማካኝነት። ስለ እውነት ከሆነ ተጫዋቾቼ ወርቅ ናቸው። በተጫዋቾቼ ነው እዚህ የደረስኩት። ከበፊት ጀምሮ የነበሩ አሁንም ያሉትን ተጫዋቾች አመሠግናለሁ። መጥተው ወርቅ ስለሰጡኝ በጣም ሰርፕራይዝድ ሆኛለሁ። የታደሙት የሚዲያ ባለሙያዎች ናቸው ፤ ቅኝት በኳስ ሜዳ ፣ ንስር ስፖርት ፣ ጋዜጠኛ ወርቅነህ ጋሻው ፣ በተጨማሪ ደግሞ ድሮ አብሮኝ በሠራው ሶፎንያስ እንየው ነው ፕሮግራሙ ሲመራ የነበረው እና አጠቃላይ የነበሩ ሰዎች ሁሉ አስደስተውኛል። ያልጠበኳቸው እና ሸልመውኝ ደስታ የፈጠሩብኝ ተጫዋቾቼ ናቸው ፣ ኮቺንግ ስታፉንም ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክንም ተጫዋቾች ወደዚህ መጥተው የፈለጉትን እንዲያደርጉ ፍቃድ በመስጠቱ አመሠግናለሁ።”
በመጨረሻም የምትለው ነገር ካለ…
“የሴቶች እግርኳስ በጣም ደስ የሚል ደረጃ ላይ ደርሷልና እንተባበር ፣ እንዋደድ ፣ እንከባበር ፣ እንፋቀር ፤ እኔ የገረመኝ ብዙ ባለሙያተኞች ፕሮግራሜ ላይ መጥተዋል። ምን ያህል መተሳሰቡ እንዳለ ተረድቻለሁ እና ያን ካደረግን የኢትዮጵያ እግርኳስ በአፍሪም በዓለም አቀፍም ትልቅ ደረጃ እንደሚደርስ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ፤ አንተም ቃለመጠይቅ ስላደረግክልኝ አመሠግናለሁ።”