የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የኢትዮጵያ ሴቶች ሊግ ስፖንሰር ማድረጉን በዛሬው ዕለት በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ተበስሯል።
ዛሬ ቀትር በኋላ በሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በተፈረመ ስምምነት ለሦስት ዓመታት የሚቆይ በዓመት ኢትዮጵያ መድን አስር ሚሊየን ብር በሦስት ዓመት ደግሞ በድምሩ ሠላሳ ሚሊየን ብርን ለፌደሬሽኑ የሚያስገኝ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ስለመሆኑም ተገልጿል።
መርሃግብሩን በመግቢያ ንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በንግግራቸው ይህ ትልቅ ተቋም እግር ኳሱን ለማገዝ በማሰብ ይህን ስምምነት በመፈፀሙ መመስገን እንደሚገባው ገልፀው ከዚህ በኋላ ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች በሴቶች እግርኳስ ውድድሮች ላይ እና በሌሎች ሁነቶች ላይ ኢትዮጵያ መድንን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ፕሬዝደንቱ አያይዘውም በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ “የመጀመሪያ” ሲሉ የገለፁት ስምምነት ከዚህ ቀደም የሴቶች እግርኳስ በጀት ከፌዴሬሽኑ የስራ ማስኬጃ በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድር እንደነበረ አንስተው የዛሬውም ስምምነት 80% ይህን ወጪ እንደሚቀንስም አንስተዋል።
በንግግራቸው ማሳረጊያም ይህ ስምምነት በ30 ሚልየን እንደማይገታ እምነት እንዳላቸው ያነሱ ሲሆን በቀጣይም ሁለቱ አካላት በተለያዩ መስኮች በጋሩ ሊሰሩባቸው የሚችሉ እንደሆነም አንስተዋል።
በማስከተል መድረኩን የተረከቡት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ነፃነት ለሜሳ ሲሆኑ
ድርጅታቸው ከ1970ዎቹ አንስቶ በእግር ኳሱ ለትርፍ ሳይሆን ማህበራዊ ኋላፊነቱን ለመጣት ብሎም እግር ኳሱን ለማሳደግ ሲንቀሳቀስ እኔደቆየ አንስተው አሁን ደግሞ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በሴቶች እግርኳስ ላይ አሻራቸውን ለማሳረፍ በትብብር ተመስራት እደመጡ ተናግረው።
አያይዘውም ድርጅታቸው የሴቶች ቡድንን ለማቋቋም የተጫዋቾች መለማመጃ እና ማረፊያ ካምፕ ለመገንባት የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኙም አንስተዋል።
ሁለቱም አካላት ንግግራቸውንን ከቋጩ በኋላ በስፍራው የተገኙት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተለያዮ ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን ዋና ዋናዎቹ በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ መድን እንደ አንጋፋነቱ የሴቶች ቡድን አለማቋቋም ምክንያቱ ምድነው ?
አቶ ነፃነት
“ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ መድን የሴቶች ቡድን ነበረው በተለይ ካምፕ ላይ ባጋጠሙን አንዳንድ ችግሮች ክለቡ በሚፈለገው ደረጃ ያልሄደበት ሁኔታ ነበር። ቅድም በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ያለን ካፕ ለወንዶች ብቻ የሚሆን ነው ፤ ስለዚህ ሴቶችን ማሳረፊያ ስለሚያስፈልግ በዚህ ምክንያት ለዘንድሮው አላዘጋጀንም። የወንዶች ቡድናችን ወደ ሊጉ ዳግም ከመጣ ሦስት አመት ነው ቡድኑን መሠረት እንዲይዝ ለማደራጀት ከፍተኛ በጀት ነው ያፈሰስነው። በዚህ እንዲሁም የካምፕ ግንባታው ትንሽ ስለለዘገየብን እንጂ ዘንድሮ ካንፑን እና ሌሎች ነገሮችን ጨርሰን የሴት ቡድን ለማቋቋም ዕቅዱ አለን።”
ስምምነቱ የጥቅም ግጭት አይፈጥረም ወይ?
አቶ ነፃነት
“የስፖንሰርሺፕ ስምምነቱ ሌላ ጎን ነው። እኛ ፋይናስ የምናደርገው ዳኞች ነጥለን ውጤት እንዲያዛቡ ወይም ደግሞ ኮሚሽነሮችን ነጥለን ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ አይደለም ስፖንሰር የምናደርገው። እኛ ሂደቱ እንዲሄድ ፌዴሬሽኑን ብቻ ነው ስፖንሰር የምናደርገው ይህ አሰራር በተለያዩ አለማት ያለ ነው። ምንም የጥቅም ግጭት ያጋጥመናል ብለን አናስብም።”
አቶ ኢሳያስ ይህን ጥያቄ ሲያብራሩ
“በክለብ ላይሰንሲግ አንቀፅ 3 ላይ መስፈርቱን አሟልተው የሚወዳደሩ ክለቦች ፓርትነር ሆነው መስራት እንደሚችሉ ይደነግጋል። በተለይ የሴቶች ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ያበረታታል። ይህ ማለት ሊጉን ስፖንሰር ስላደረጉ ዝም ብለው እዚህ ውስጥ ይቀጥላሉ ማለት አይደለም። ያኛውንም ካሳ ለመቀበል አይደለም። ፌዴሬሽኑ የኢንሹራንስ ካምፓኒ አይደለም። የተፈራረምነው ከኢንሹራንስ ድርጅት ጋር ነው። ስለዚህ እዚህ መሀል ምንም አይነት የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ነገር የለም። መሰረታዊው ነገር የመጣውን መልካም አጋጣሚ ማድነቅ አለብን። ማነው በዚህ ደረጃ ደፍሮ የመጣው ይህ ሊደነቅ ይገባል። እነ ዋልያ እኮ ብሔራዊ ቡድኑን ጥለው ወጥተዋል። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ተቋማት እግርኳሱን በማገዝ እንዲበራከቱ ነው የሚፈለገው። መሰል ተቋማት ተቀናጅተው ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ነው። ዋናው ብሔራዊ ቡድን ከሀገር ውጭ በመጫወቱ ፌዴሬሽኑ ብዙ ዋጋ እየከፈለ ነው። ስለዚህ መበረታታት አለበት። መድን እግርኳስ ክለብ ባይኖረው እስቲ ብለን እናስብ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማድረጉ ማመስገን ያስፈልጋል።” ሲሉ ተደምጠዋል።