የታንዛንያ ብሔራዊ ቡድን ከ18 ዓመታት ቆይታ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ረቷል።
ታንዛንያዎች ባደረጓቸው ፈጣን ጥቃቶች የጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ ‘የታይፋ ስታርስ’ የጨዋታ እንዲሁም የሙከራ ብልጫ የታየበት ነበር ፤ ምብዌና ሳማታ ከግራ መስመር አሻምቷት በነፃ አቋቋም የነበረው ሳይሞን ሙሱቫ በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም ክሌመንት ምዚዜ ከአማካይ ክፍል የተላከችለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሰይድ ሀብታሙ በጥሩ ብቃት ያዳናት ኳስም ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው።
በአስራ አምስተኛው ደቂቃ ግን ሦስት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ያደረጉት ታንዛንያዎች መሪ የምታደርጋቸው ግብ አስቆጥረዋል ፤ ኖቫቱስ ሚሮሺ ከማዕዝን ምት አሻምቷት ሳይሞን ሙሱቫ በግንባሩ ያስቆጠራት ኳስም ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ነች።
ከግቧ መቆጠር በኋላም ዕድሎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት ታንዛንያዎች በሰላሣ አንደኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ የሚያደርጉበት ግብ አስቆጥረዋል። ሙዳትሂሪ አባስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ አከባቢ አሻምቷት ፋይሰል አብደላ በግንባሩ ገጭቷት ሰይድ ሀብታሙ ካዳናት በኋላ ፋይሰል አብደላ የተመለሰችውን ኳስ ተጠቅሞ በግምባሩ ያስቆጠራት ኳስም ‘የታይፋ ስታርስ’ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገች ግብ ነበረች።
በአጋማሹ ሁለት ሙከራዎች ብቻ በማድረግ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው ዋልያዎቹ አብዱልከሪም ወርቁ ከቢንያም በላይ የተቀበላቸውን ሁለት ኳሶች ተጠቅሞ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል የጠራ ዕድል መፍጠር አልቻሉም።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተጫዋቾች ቅያሪ አድርጎ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መያዝ ቢችልም ሙከራዎች በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ግን ታንዛንያዎች ነበሩ። ግብ አስቆጣሪው ሳይሞን ሙሱቫ በተከላካዮች የቦታ አያያዝ ችግር ያገኛት ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሯት ምብዌና ሳማታ ሳይጠቀምባት የቀረው ወርቃማ ዕድልም ተጠቃሽ ሙከራ ነች። ዋልያዎቹ በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም የታንዛንያ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፤ ሆኖም በረከት ደስታ ከያሬድ ባየህ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ እንዲሁም አንተነህ ተፈራ ከበረከት ወልዴ የተላከችለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
የታንዛንያ ብልጫ የታየበት ጨዋታው የታይፋ ስታርስ በመጀመርያው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ታግዘው ጨዋታውን በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋቸውን ስያለመልሙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከማጣርያ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል።
ውጤቱን ተከትሎ የታንዛንያ ብሄራዊ ቡድን ከአስራ ስምንት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን መርታት ችላለች፤ የታይፋ ስታርስ ለመጨረሻ ጊዜ በ1999 ዓ.ም ሕዳር 16 ዋልያዎቹን ሁለት ለአንድ ማሸነፋቸውን ይታወሳል ፤ ቢንያም አሰፋ ለኢትዮጵያ አሚር ሙፍታሕ እና አድሚን ባንቱ ደግሞ ለታንዛንያ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾችም ነበሩ።