በሞሮኮ እየተደረገ ባለው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሦስተኛ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በግብፁ ማሳር ሦስተኛ ሽንፈታቸውን በማስተናገድ ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።
የምድብ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከሰንዳውንሱ የ4ለ0 ሽንፈታቸው የአራት ተጫዋቾች ለውጥን ሲያደርጉ አበባ አጄቦ ፣ ድርሻዬ መንዛ ፣ ሒሩት ተስፋዬ እና ንግስት በቀለ አርፈው ታሪኳ በርገና ፣ ሳራ ነብሶ ፣ ናርዶስ ጌትነት እና ሰናይት ቦጋለ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ተክተዋቸው ገብተዋል።
እጅግ የተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴን ባስተዋልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሀያ ያህል ደቂቃዎች በመጠኑም ቢሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመስመር በመነሳት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በይበልጥ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም የነበራቸው ደካማ አፈፃፀም የኋላ ኋላ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
በ8ኛው ደቂቃ ከግራ የተነሳችው ሳራ ነብሶ በረጅሙ የተጣለላትን ኳስ በጥልቀት ይዛ ገብታ ያደረገችው ሙከራ በግብ ዘቧ ሀቢባ ኢማድ ሳብሪ ተመልሶባታል ፣ መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት በቀጥታ መታ በቀላሉ በግብ ዘቧ ከተያዘባት በኋላ በመልሶ ማጥቃት በቀላሉ ወደ ተቃራኒ ሜዳ መግባት የጀመሩት ማሳሮች በመጀመሪያ ሙከራቸው ከጎል ጋር ተገናኝተዋል።
21ኛው ደቂቃ ላይ ሳንድሪኔ ኒዮንኩሩ መሐል ለመሐል ከተከላካዮች ሾልኮ የደረሳትን ኳስ ታሪኳ በርገና ብትመልስባትም በድጋሚ የተመለሠችዋን ኳስ መረቡ ላይ አሳርፋ ቡድኗን ቀዳሚ አድርጋለች። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ መጠነኛ መነሳሳት አሳይተው በሴናፍ አማካኝነት ጥሩ ዕድልን ለመፍጠር የሞከሩት ንግድ ባንኮች ጥረት ቢያደርጉም የተጋጣሚያቸውን የመከላከል አጥር ማስከፈቱ ላይ ግን ውስንነት ነበረባቸው። አጋማሹ ሊቋጭ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ማሳሮች በተደጋጋሚ ለተጨማሪ ጎሎች ቢቃረቡም አጋማሹ በ1ለ0 ውጤት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ዳግም በቀጠለው ጨዋታ ተመጣጣኝ የሚመስል የሜዳ ላይ አጨዋወቶችን ብናይም በመልሶ ማጥቃት ስል የሆኑት ማሳሮች ግን በተደጋጋሚ የንግድ ባንክን የኋላ በር በማንኳኳት የተሻሉ ነበሩ። ያሲሚን መሐመድ ባደረገችው እና ታሪኳ በርገና በመከተችው ሙከራ በአጋማሹ ቀዳሚ የሆኑት ማሳሮች ከደቂቃ ደቂቃ የነበራቸው የጨዋታ ብልጫ ያለቀላቸውን ዕድሎች ሲፈጥሩ ቢታዩም የግብ ዘቧ ታሪኳ በርገና ድንቅ ብቃቶች የተደረጉ ሙከራዎች ወደ ጎልነት እንዳይለወጡ ስታደርግ ተስተውሏል።
የጎል ዕድሎችን በመፍጠሩ ፍፁማዊ ብልጫ የነበራቸው ማሳሮች ካደረጓቸው በርካታ ሙከራዎች በኋላ 86ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ አንድ ሁለት ሀስናትስ ሊጉስ ሞክራ በታሪኳ የተተፋን ኳስ ያስሚን መሐመድ በቀላሉ ከመረብ አሳርፋለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ወደ ጨዋታው በይበልጥ የገቡት ንግድ ባንኮች ታሪኳ ዴቢሶ ከቀኝ በረጅሙ ያሻገረችውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ ወደ ጎልነት ብትቀይረው ጨዋታው ግን በመጨረሻም በማሳር የ2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
ውጤቱን ተከትሎ የግብፁ ክለብ ማሳር ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፍ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።