መረጃዎች | 30ኛ የጨዋታ ቀን

በ8ኛው ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የሚደረጉ መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በደረጃ ሰንጠርዡ ከፍ ለማለት የሚፋለሙ ፤ በሁለት ነጥብ የሚበላለጡ ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

ከተከታታይ አራት ድሎች በኋላ በባህርዳር ከተማ ሽንፈት በማስተናገድ የሊጉን መሪነት አሳልፈው የሰጡት ሲዳማ ቡናዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ፈረሰኞቹን ይገጥማሉ።

ሲዳማ ቡናዎች በድራማዎች ታጅቦ በተካሄደው እና ተጋጣሚያቸው ባህርዳር ከተማ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች ባመከነበት የመጨረሻው የሊጉ ጨዋታቸው ላይ ከወትሮው የተዳከመ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።

በተለይም በአራት መርሃግብሮች ስድስት ግቦች ማስቆጠር የቻለው የፊት መስመሩ በጨዋታው አደጋዎች መፍጠር ሳይችል ቀርቶ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥር ወጥቷል። በነገው ዕለትም በመጨረሻዎቹ ሁለት መርሃግብሮች መረቡን ሳያስደፍር ለወጣው እና በጥሩ የለውጥ ሂደት ላለው የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ ክፍል የሚመጥን አቀራረብ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።

በመቐለ 70 እንደርታ ከደረሰባቸው ሽንፈት በማገገም ሁለት ድሎች እና አንድ የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት ፈረሰኞቹ ነጥባቸው አስር በማድረስ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሰባቱን ከማሳካታቸውም በዘለለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸው ተሻሽሏል። በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ካስተናገዱ ወዲህ በመጨረሻዎቹ መርሃግብሮች መረቡን ሳያስደፍር የወጣው የመከላከል አደረጃጀትም በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የማጥቃት አጨዋወቱም አሁንም የአፈፃፀም ችግሮቹን መቅረፍ የሚጠበቅበት ቢሆንም በጥሩ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኑ አይካድም። ሆኖም በነገው ዕለት በጨዋታ በአማካይ ከአንድ ግብ በታች(0.6) ያስተናገደ እና ከኢትዮጵያ መድን እና ባህርዳር ከተማ ቀጥሎ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደመግጠሙ የአፈፃፀም ክፍተቱን አርሞ መቅረብ ይኖርበታል።

ሲዳማ ቡናዎች ከቅጣትም ሆነ ጉዳት ነፃ የሆነው ስብስብ ይዘው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በረከት ወልዴ በቅጣት አይሰለፍም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 28 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው በአንፃሩ ሲዳማ ቡና ሁለት ጊዜ አሸንፏል። ስምንት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 39 ሲዳማ ቡና ደግሞ 12 ጎሎችን አስመዝግበዋል።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

በአንድ ነጥብ የሚበላለጡ የቅርብ ተፎካካሪ ቡድኖች የሚያገናኘው እና ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው መርሃግብር የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ነው።

በሊጉ የመጀመርያው መርሃግብራቸው በስሑል ሽረ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ በአራት ጨዋታዎች ሽንፈት አልባ ጉዞ ያደረጉት አዳማዎች በመጨረሻው መርሃግብር በመቻል ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ይገጥማሉ።

በውድድር ዓመቱ በጨዋታ በአማካይ 1.3 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ቡድኑ ሁለት ሁለት የድል፣ የአቻ እና የሽንፈት ውጤቶች በእኩሌታ በማስመዝገብ ከነገው ተጋጣሚው መድን በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ስምንት ነጥቦችን ሰብስቧል።

በነገው ጨዋታም ከሽንፈቱ ቶሎ ለማገገም እንዲሁም ደረጃውን ለማሻሻል በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙት መድኖች ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሦስት ግቦች አስተናግዶ ዓመቱን ከጀመረ በኋላ ጠንካራ ክለቦችን በገጠመባቸው በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን በማስተናገድ አንፃራዊ መሻሻል አሳይቶ የነበረው ቡድኑ በመጨረሻው መርሃግብር የታየበትን መጠነኛ የመከላከል ድክመት ቀርፎ መግባት ግድ ይለዋል።

በአራት ጨዋታዎች  ድል አልባ ጉዞ በማድረግ ያልተጠበቀ አጀማመር ማድረግ ችለው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ተከታታይ ሁለት ድሎች በማስመዝገብ እፎይታ አግኝተዋል።

ኢትዮጵያ መድን እስካሁን ድረስ በክፍት የጨዋታ ሂደት ግብ ባለማስተናገድ የመከላከል ጥንካሬውን አስመስክሯል። ካከናወናቸው ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ መረቡን ባለማስደፈር የማይቀመስ የመከላከል አደረጃጀት የገነባው ቡድኑ በሂደት የፊት መስመር ክፍተቱን በማረም ግቦችንም ማስቆጠር ጀምሯል። በመጨረሻው መርሃግብር መቐለ 70 እንደርታን አራት ለባዶ በማሸነፍ የተከታታይ ሳምንታት የግብ ርሀባቸው ያስታገሱት መድኖች በነገው ጨዋታ የተለመደው የመከላከል ጥንካሬያቸው ከማስቀጠል በዘለለ በሂደት ወደ ጥሩ ቁመና የመጣውን የፊት መስመር ውጤታማነታቸው ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

በአዳማ ከተማ በኩል ዳንኤል ደምሱ አሁንም በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም፤ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራም በጉዳት የመሰለፍ ነገር አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ 21 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዳማ 7 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። መድን 4 ሲያሸንፍ 11 ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ ፤ አዳማ 26 ሲያስቆጥር መድን 24 አስቆጥረዋል። የመጨረሻው ግንኙነትም ኢትዮጵያ መድን ከ 20 ዓመታት በኋላ አዳማ ከተማን ያሸነፈበት ነበር።