ሪፖርት | ሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርተዋል

የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ጎል ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።

ሲዳማ ቡናዎች በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ አሰላለፍ ደስታ ዮሐንስ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ሬድዋን ናስር እና ፍቅረየሱስ ተተወልደብርሃንን አስወጥተው በፍራኦል መንግሥቱ፣ አስቻለው ሙሴ፣ ኢማኑኤል ላርዬ እና በዛብህ መለዮ ተክተው ሲገቡ ፈረሰኞቹ አዞዎቹን ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ይዘው የቀረቡበት እና ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት የመጀመርያው አጋማሽ ተቀራራቢ የሚባል የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢታይበትም ሲዳማ ቡናዎች ሙከራዎች በማድረግ ረገድ የተሻሉ ነበሩ።

ቡድኑ ከፈጠራቸው ሙከራዎችም መስፍን ታፈሰ ግብ ጠባቂው በረዥሙ አሻምቷት ሀብታሙ ታደሰ የጨረፋት ኳስ አግኝቶ በመምታት የግቡ ቋሚ የመለሰበት እንዲሁም በዛብህ መለዮ ከመስፍን ታፈሰ የተሻገሩ ሁለት ኳሶች አግኝቶ ባህሩ ነጋሽ በሚያስደንቅ ብቃት ያዳናቸው ሁለት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ከተጋጣሚያቸው ጋር ተቀራራቢ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መያዝ ቢችሉም ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ብልጫ የተወሰደባቸው ፈረሰኞቹም ሻሂዱ ሙስጠፋ ከቆመ ኳስ አክርሮ መቷት ቶም ኢካራ በመለሳት እንዲሁም በቶሎሳ ንጉሴ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል፤ ተከላካዩ ከአማኑኤል ኤርቦ የተቀበላትን ኳስ መቶ ለጥቂት የወጣችው ኳስም የተሻለች ለግብ የቀረበች ነበረች።

ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ እንዲሁም ሙከራዎች በማድረግ ተሽለው የታዩበት ነበር። ፍሪምፖንግ ክዋሜ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቷት ቶም ኢካራ እንደምንም የመለሳት፣ አማኑኤል ተርፋ ቴሎሳ ንጉሴ ከመዓዘን ምት ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ያደረጋት ሙከራ እንዲሁም ከግቡ አፋፍ የነበረው መሐመድ ኮኔ ፍፁም ጥላሁን በግሩም ሁኔታ ወደ ሳጥን ገብቶ አሻግሯት ወደ ግብነት ያልቀየራት ኳስ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁሉም መለኪያዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የወረደ እንቅስቃሴ ያሳዩት ሲዳማ ቡናዎችም በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ሀብታሙ ታደሰ አምበሉ ያሬድ ባየህ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ላይ ያገኛትን ኳስ አሻግሮለት ከተከላካዮች ጋር ታግሎ መቷት ባህሩ ነጋሽ ያዳናት ኳስም ቡድኑም የማታ ማታ አሸናፊ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

ጨዋታው ባዶ ለባዶ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በአስራ ሦስት ነጥቦች ከመሪው ጋር በነጥብ ሲስተካከል ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን አስራ አንድ አድርሰዋል።